የጥምቀት እና የከተራ በዓል ስኬታማ ነበር።

11
ባሕር ዳር: ጥር 13/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ‎የከተራ እና የጥምቀት በዓል በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች በድምቀት መከበሩን የአማራ ክልል ባሕል፣ ቱሪዝም እና ስፖርት ቢሮ አስታውቋል፡፡
የአማራ ክልል ባሕል፣ ቱሪዝም እና ስፖርት ቢሮ ኀላፊ መልካሙ ጸጋዬ በዓሉን ለማክበር ወደ ዓደባባይ የወጣው ሕዝብ እና ቱሪስቶች በዓሉን በደመቀ ሁኔታ አክብረዋል ብለዋል።
ካለፉት ሁለት ዓመታት በተለየ ሁኔታ በዓሉ በደማቅ ሁኔታ የተከበረበት፣ በርካታ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ሀገር ቱሪስቶች የተገኙበት እና ማኅበረሰቡም ፍጹም ሰላማዊ በኾነ መንገድ በነቂስ ወጥቶ ያከበረበት በዓል ነበር ነው ያሉት ኀላፊው።
‎የከተራ እና የጥምቀት በዓላት ቱሪስቶች ወደ ክልሉ እንዲመጡ የነበረው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነበር። ለአብነትም ቀደም ብሎ ከቱሪዝም ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት መደረጉን አስታውሰዋል።
‎አስጎብኝ ድርጅቶች ለቱሪስቶች በክልሉ የጉብኝት ፖኬጆችን እንዲሸጡ ሥራዎች ተሠርተው ነበር ነው ያሉት። ቱሪስቶች ሲመጡ በአገልግሎት ሰጭ ተቋማት ተገቢውን አገልግሎት እንዲያገኙ ባለሙያዎችን በማሠልጠን እና አገልግሎቶች ዋጋቸው ተመጣጣኝ እንዲኾን በሰፊው ተሠርቷል ብለዋል።
‎ክብረ በዓላትን እና የቱሪስት መዳረሻ ቦታወችን በተለያዩ የሚዲያ አማራጮች የማስተዋወቅ ሥራ ተሠርቷል ብለዋል። በዓላቱ የሚከበሩባቸውን ቦታዎች ቀድሞ ለማመቻቸት፤ ሳቢ እና ማራኪ ለማድረግ ከፍተኛ ጥረት መደረጉንም ገልጸዋል። ይህ በመኾኑም “የጥምቀት እና የከተራ በዓል ስኬታማ ነበር” ነው ያሉት።
‎በተሠሩ ሥራዎችም ከፍተኛ ቁጥር ያለው ቱሪስት ወደ ክልሉ መጥቷል፤ በሁሉም የክልሉ ዋና ዋና ከተሞች የውጭ ሀገር ቱሪስቶች መታደማቸውንም ጠቁመዋል።
‎በቀጣይ ለሚከበሩ ሃይማኖታዊ እና ሕዝባዊ በዓላት በእንጅባራ የአገው ፈረሰኞች በዓል፣ በባሕር ዳር ለሰባሩ ጊዮርጊስ፣ መርጡ ለማርያም አስተርዮ፣ በደብረ ታቦር እና መካነ ኢየሱስ የመርቆርዮስ በዓላት ቱሪስቶች እንዲመጡ አስጎብኝ ድርጅቶች ሚናቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል።
‎የጸጥታ ኃይሎች በዓላት በሰላም እንዲከበሩ ሢሠሩ የቆዩትን ሥራ አጠናክረው እንዲቀጥሉም ጠይቀዋል። ማኅበረሰቡም በዓላቶቹን ባሕላዊ እሴቶቻቸውን ጠብቀው በማክበር እና እንግዶችን ተቀብሎ በማስተናገድ የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ መልዕክት አስተላልፈዋል።
‎ዘጋቢ፦ ፍሬሕይዎት አዘዘው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous article‎ጥምቀት ምንድን ነው? ለምንስ በውኃ ኾነ? ‎
Next articleየአንድ ተማሪ የፈተና ውጤት የተማሪው፣ የወላጅ እና የመምህራን የጋራ ጥረት ነው።