‎ጥምቀት ምንድን ነው? ለምንስ በውኃ ኾነ? ‎

10

ባሕር ዳር: ጥር 12/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ‎‌ጥምቀት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ተከታዮች ዘንድ በድምቀት የሚከበር በዓል ነው፡፡ በዓሉ በድምቀት ከመከበር ባለፈ ታላቅ ሃይማኖታዊ ምስጢርም ያለው ነው፡፡

‎የቃሉ ትርጉም ጥምቀት ማለት “አጥመቀ” ከሚለው የግዕዝ ቃል የተገኘ ሲኾን ትርጉሙም በውኃ ውስጥ መዘፈቅ ወይም መነከር ማለት ነው።

ሃይማኖታዊ አስተምህሮውስ ምንድን ነው?

‎በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በደቡብ ጎንደር ሀገረ ስብከት በደብረ ታቦር ደብረ ልዑላን መድኃኔዓለም የአራቱ ጉባኤያት መጻሕፍት መምህር የኾኑት መምህረ መምህራን በጽሃ አለሙ ጥምቀት በሥላሴ ስም በውኃ ተጠምቆ የእግዚአብሔር ልጅ መኾን፣ ኃጥያትን መታጠብ እና መንፈስ ቅዱስን መቀበል እንደኾነ ነግረውናል፡፡

‎የጥምቀት በዓል ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ከፈጸማቸው የማዳን ጉዞዎች መካከል አንዱ እና የሥራ መጀመሪያም ነው ይላሉ፡፡ የኢየሱስ ክርሰቶስ ጥምቀት እሱ ሊጠቀምበት ሳይኾን የሰዎችን ጥምቀት ለመባረክ የተደረገ መኾኑን ነው የገለጹት፡፡

‎ሰማይ ሲከፈት ታያላችሁ ተብሎ እንደተነገረው ክርስቶስ ሲጠመቅ ሰማይ ተከፍቶ እግዚአብሔር አብ በደመና “የምወደው ልጄ ይህ ነው እርሱን ስሙት”ብሎ የተናገረበት፣ መንፈስ ቅዱስ በእርግብ አምሳል በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ የወረደበት እና ወልድ በተለየ አካሉ በዮርዳኖስ ወንዝ የተጠመቀበት ነው ብለዋል፡፡ ይህም የሥላሴ አንድነት እና ሦስትነት የተገለጠበት እንደኾነም ነው የተናገሩት።

‎ኢየሱስ ክርስቶስ በዮርዳኖስ ወንዝ ተጠምቆ ጥምቀትን ለሰው ልጆች ሁሉ በይፋ ከፍቷል፡፡ በዮርዳኖስ ወንዝ የነበረውን የአዳም እና የሄዋን የዲያቢሎስ የባርነት የዕዳ ደብዳቤ በአምላክነቱ አቅልጦ ያጠፋበት መኾኑን ነው ያስረዱት፡፡

ጥምቀት የአዳም እርግማን የተደመሰሰበት እና የነጻነት አዋጅ የታወጀበት ነውም ብለዋል፡፡

‎ቤተክርስቲኗ ሥራዎቿ፣ በዓላቶቿ እና አስተምህሮዎቿ ከክርስቶስ ተግባራት የተነሱ ናቸው ነው ያሉት መምህሩ። ጥምቀት ሲከበር ክርስቶስ ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ ሄዶ መጠመቁን ለማስታወስ ታቦታቱን ከማደሪያቸው ወደ ባሕረ ጥምቀቱ በማውረድ በተግባር እያሳየች በታላቅ ድምቀት እንደምታከብርም ገልጸዋል፡፡

‎የጥምቀት ምሳሌነቱ ከብሉይ ኪዳንም የሚመዘዝ ነው፤ በብሉይ ኪዳን ለመስዋዕት የሚመረጠው በግ ከመሰዋቱ በፊት በውኃ ታጥቦ የሚሰዋው ካህን በበጉ ላይ እጁን ይጭናል፤ ወደ መስዋዕትነት ቀርቦ ይሰዋል ነው ያሉት፡፡

‎ክርስቶስም እንደመስዋዕቱ በግ በውኃ ተጠምቆ መጥምቁ ዮሐንስ እጁን ጫነበት ከዚያ በኋላ ለሰው ልጆች ኃጥያት ራሱን መስዋዕት አድርጎ መቅረቡን አንስተዋል፡፡

‎ጥምቀት ምስጢራዊ አስተምሮው ሰዎች ሁለተኛ የሚወለዱበት፤ የእግዚአብሔር ልጅነትን የሚያገኙበት እና ሰማያዊ ጉዞ የሚጀመርበት መኾኑንም አስረድተዋል፡፡

‎ክርስቶስ ውኃን የመረጠበት የራሱ ምክንያትም አለው ይላሉ መምህሩ፡፡ የውኃ ግብሩ ማንጻት በመኾኑ ጥምቀትም ለማንጻት መኾኑን አንስተዋል፡፡

ወተት ወይም የማር ወለላ ተክል ላይ ቢደረግ ያደርቀዋል፤ ውኃ ሲነካው ግን ይለመልማሉ፤ የሰው ልጆች ነፍስም የምትነጻው በውኃ ስትጠመቅ ነው ብለዋል፡፡

‎የሰው ልጅም ሰውነቱን ለእግዚአብሔር የተቀደሰ አድርጎ ለማቅረብ በውኃ መጠምቅ በማስፈለጉ እና አብነት ለመኾን እንደኾነ ነው የገለጹት፡፡

‎ሌላው በውኃ የመጠመቅ ምክንያት ውኃ ለሁሉም ሰው በቀላሉ የሚገኝ በመኾኑ እና ያለአድሎ መጠመቅ እንዲችሉ ለማድረግ ነው ብለዋል። በብሉይ ኪዳን በውኃ የስጋ ፈውስ ይደረግበት የነበረው በሀዲስ ኪዳን የነፍስ እና የስጋ ድኅነትን ለመግለጽ እንደኾነ ነው የገለጹት፡፡

‎በመጨረሻም መምህሩ የጥምቀት በዓል እግዚአብሔር የከበረበት የሰው ልጅም የተቀደሰበት በዓል በመኾኑ ምዕመኑ በባለቤትነት እንዲያከብረው አሳስበዋል፡፡

‎በዓሉ የእግዚአብሔር በዓል ነው፤ የሰላም እና የፍቅር በዓል በመኾኑ እግዚአብሔርን በማመስገን ብቻ እንዲከበር በአጽንኦትም ተናግረዋል።

‎ዘጋቢ፡- ፍሬሕይወት አዘዘው

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሲቢኢ ኮኔክት ዲጂታል ዋሌት የተሰኘ መተግበሪያ በይፋ አስጀመረ።