
አዲስ አበባ፡ ጥር 12/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በዛሬው ዕለት ስታር ፔይ ፋይናንሻል ሶሊውሽን ከተባለ ሀገር በቀል የቴክኖሎጂ ኩባንያ ጋር በመተባበር ሲቢኢ ኮኔክት ዲጂታል ዋሌት የተሰኘ የፍይናንስ አገልግሎት መስጫ መተግበሪያም በይፋ አስጀምሯል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዝዳንት ተወካይ እና የኮርፖሬት አገልግሎቶች ምክትል ዳይሬክተር ኤፍሬም መኩሪያ እንዳሉት ባንኩ ያስጀመረው የሲቢኢ ኮኔክት ዲጂታል ዋሌት መተግበሪያ የዓለም አቀፍ ደምበኞችን ፍላጎት ለማርካት እና የሀገራችንን የውጭ ምንዛሬ ግኝት ለማሳደግ ወሳኝ እርምጃ ነው።
ይህ የዋሌት መተግበሪያ ዓለም አቀፍ ደረጃውን ያሟላ፣ ደህንነቱ የተጠበቀ እና አስተማማኝ ከመሆን ባሻገር ባንኩን አዲስ አይነት የዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎት መድረክ በማስተዋወቅና በተመጣጣኝ ዋጋ የውጭ ምንዛሬ የሀዋላ አገልግሎት ለመስጠት እንደሚያግዝ ተናግረዋል።
ባንኩ መተግበሪያውን ጥቅም ላይ ማዋሉ ሕገ ወጥ የውጭ ምንዛሬን ለመከላከል እና ዜጎች ሕጋዊ መንገድን እንዲጠወሙ የሚያበረታታ ነውም ብለዋል። ለሀገራችን የልማት ተግባር በቂ የውጭ ምንዛሬ አቅርቦትም እንዲኖር ትልቅ ድርሻ ያበረክታል።
ይህ መተግበሪያ እንደ ሲቢኢ ብር እና ቴሌ ብር ከመሳሰሉት ዋሌቶች በተለየ መልኩ ብዙ አይነት የውጭ ሀገር መገበያያ ገንዘቦችን ለመላክና ወደ ብር ለመመንዘር በብር ሂሳብ ኢትዮጵያ ውስጥ በቀጥታ ለመጠቀም ያስችላል ነው ያሉት።
መተግበሪያው ለኢትዮጵያ ዲያስፖራ አባላት ድንበር ተሻጋሪ የገንዘብ መላላኪያና የውጭ ምንዛሬ ከማቅረብ ባለፈ የቤትና የመኪና ብድር አገልግሎት ለማቅረብም ያስችላል።
ሲቢኢ ኮኔክት ዲጂታል መተግበሪያ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያዊ ከሆኑ ባንኮች ጋርም የተሳሳረ መሆኑ የዚህ ዋሌት መለያ እንደሆነም ገልጸዋል።
መተግበሪያው በባንኮች መካከል ቅፅበታዊ የገንዘብ ዝውውር ለመፈጸም ያስችላል፤ ዓለም አቀፍ የውክልና አገልግሎት ጥቅም ላይ ያውላል፤ በዓለም አቀፍ የክፍያ ካርዶችም ገንዘብ ለመላክ ያስችላል ብለዋል።
ዘጋቢ፦ አፈወርቅ አበዶም
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
