የትምህርት ጥራት ለመረጋገጥ በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን እንደሚወጡ ኑሮአቸውን በውጭ ሀገራት ያደረጉ ኢትዮጵያውያን አስታወቁ።

13

ጎንደር: ጥር 12/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የጎንደር ዩኒቨርሲቲ “ኑ ሀገር የሚገነቡትን እንገንባ” በሚል መሪ መልዕክት የዩኒቨርሲቲውን ሞዴል ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በተመለከተ ኑሯቸውን በውጭ ሀገራት ካደረጉ ኢትዮጵያውያን ማኅበረሰብ አካላት ጋር ውይይት አካሂዷል።

በውይይቱ መነሻ ጽሑፍ ቀርቧል። በሀገር አቀፍ ደረጃ በርካታ ዲያስፖራዎች ትምህርት ቤቶችን በመገንባት፤ የትምህርት መስጫ ቁሳቁሶችን በማሟላት እና በተለያዩ ዘርፎች ድጋፍ እያደረጉ እንደሚገኙ በጽሑፉ ተነስቷል።

የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ሞዴል ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በ2015 ዓ.ም ከ9 እስከ 12ኛ ክፍል የኾኑ 50 ተማሪዎችን በመቀበል ሥራ የጀመረ ሲኾን አሁን ላይ 240 ተማሪዎችን እያስተማረ እንደሚገኝ በዕለቱ ተገልጿል።

የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት አሥራት አጸደወይን ኅብረተሰቡ መሪ የልማት ተሳታፊ ኾኖ ትምህርት ቤቶችን በመገንባት እና በመደገፍ ለትምህርት ጥራት መረጋገጥ መሥራት አለበት ብለዋል። ከጨለማ ወደ ብርሃን ለማቅናት ተማሪዎችን እና ትምህርት ቤቶችን መደገፍ ያስፈልጋል ነው ያሉት።

የማኅበረሰብ ትምህርት ቤት በማቋቋም፤ የትምህርት ቁሳቁሶችን በማሟላት፤ መምህራንን በመደገፍ እና የማጠናከሪያ ትምህርቶችን በመስጠት ተማሪዎችን ለማብቃት ዩኒቨርሲቲው እየሠራ ነው ብለዋል።

ትምህርት ቤቱን ከማቋቋም ጀምሮ ድጋፍ እያደረጉ ለሚገኙ አካላትም ምስጋና አቅርበዋል። ዩኒቨርሲቲው ሀገር የገጠማትን የትምህርት ጥራት ቸግር ለመቅረፍ የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ ነው ብለዋል።

በውጭ ሀገራት ኑሯቸውን ያደረጉት ግለሰቦች የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ሞዴል ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤትን በሚችሉት ሁሉ እንዲደግፉ ጥሪ አቅርበዋል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች የትምህርት ጥራት እንዲረጋገጥ የበኩላቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል። በውጭ ሀገራት የሚኖሩ የምክክሩ ተሳታፊዎች የማኅበረሰብ ትምህርት ቤቶችን እና ተማሪዎችን ለማገዝ እንደሚሠሩ ቃል ገብተዋል።

ዩኒቨርሲቲው የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ የሚያከናውነውን ተግባር አጠናክሮ እንዲቀጥልም አሳስበዋል።

ለተማርንበት አካባቢ እና ለሀገራችን የትምህርት ጥራት መረጋገጥ መሥራት አለብን ነው ያሉት ዲያስፖራዎቹ። የትምህርት ጥራት የሚረጋገጠው በቴክኖሎጅ ሲታገዙ በመኾኑ ተማሪዎች ውጤታማ እንዲኾኑ እገዛ ለማድረግ የበኩላቸውን እንደሚወጡም ተናግረዋል።

ዘጋቢ:- ያየህ ፈንቴ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“በሙሽርነቷ ያለች፤ በክብሯ የኖረች”
Next articleየኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሲቢኢ ኮኔክት ዲጂታል ዋሌት የተሰኘ መተግበሪያ በይፋ አስጀመረ።