“በሙሽርነቷ ያለች፤ በክብሯ የኖረች”

8

ባሕር ዳር: ጥር 12/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ጎንደር ዛሬም እንደታጀበች፤ ዛሬም እንደተከበረች፤ ዛሬም በታቦታቱ እንደተባረከች፤ እንደተቀደሰች እና በረከትን እንደተቀበለች ናት።

ጎንደር ዛሬም በሰው እንደተመላች፤ በሊቃውንቱ እንደደመቀች፤ በእንግዶች እንደተዋበች ናት።ሰፊው እልፍኟ፣ እንግዳ በቃኝ የማይለው አዳራሿ ዛሬም በእንግዶች እንደተመላ ነው።

በጥምቀት ከተራ የደመቀችው፤ በጥምቀት ክብሯን የገለጠችው የጥሯ ሙሽራ፣ የጥምቀት ሠርገኛዋ ጎንደር ዛሬም በቃና ዘገሊላ በዓል እንደደመቀች ናት። የታሪክ አምባዋ፤ የአብያተ መንግሥታቱ መገኛ፤ የነገሥታቱ መናገሻ፤ የሊቃውንቱ መመላለሻ ጎንደር በጥር ትደምቃለች። በጥምቀት ትዋባለች።

ከወርኃ ጥር መጀመሪያ ጀምራ መድመቅ የምትጀምረው ጎንደር በከተራ፣ በጥምቀት እና በቃና ዘገሊላ በዓላት ደግሞ በሰው ትመላለች። ነጫጭ በለበሱ ምዕመናን ትሸፈናለች። እነኾ ይህ ከኾነ ቀናት ተቆጥረዋል። የጎንደር ጎዳናዎች በሰው ከተመሉ ሰነባብተዋልና።

ዝማሬ እና እልልታ ከጠዋት እስከማታ አይለያትም። ሊቃውንቱ ይዘምራሉ፤ ምዕመኑ እልልታውን ያስተጋባሉ፤ መለከቱ ይነፋል፤ ነጋሪቱ ይጎሰማል፤ ጎበዛዝቱ እና ወይዛዝርቱም አምረው እና ተውበው ባማሩት ጎዳናዎች ይመላለሳሉ።

“በሙሽርነቷ ያለችው፤ በክብሯ የኖረችው” ጎንደር ዛሬም እንደተዋበች እና እንደደመቀች በዓሏን እያከበረች፤ እንግዶቿን እያስተናገደች ነው።

በታርቆ ክንዴ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleከ1 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት አደንዛዥ እጽ ተያዘ።
Next articleየትምህርት ጥራት ለመረጋገጥ በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን እንደሚወጡ ኑሮአቸውን በውጭ ሀገራት ያደረጉ ኢትዮጵያውያን አስታወቁ።