ከ1 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት አደንዛዥ እጽ ተያዘ።

5

ሁመራ: ጥር 12/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ከ1 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት አደንዛዥ እጽ ሲዘዋር በቁጥጥር ስር ማዋሉን በአማራ ክልል የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ጠቅላይ ፖሊስ መምሪያ አስታውቋል።

አደንዛዥ እጹ የጥምቀት በዓልን ተገን በማድረግ እና የጸጥታ ኃይሉ በበዓል ስምሪት ሊዘናጋ ይችላል በሚል ሀሳብ ሳይዘዋወር እንዳልቀረ የጠቅላይ ፖሊስ መምሪያው ዋና አዛዥ ኮማንደር ወለላው ተገኘ ገልጸዋል።

ይሁን እንጂ የዞኑ የጸጥታ አካላት ተግባራቸውን በሁሉም አቅጣጫ እያከናወኑ ነበር ብለዋል።

የተያዘው አደንዛዥ እጽም ሀሽሽ መኾኑን ያስረዱት ኮማንደር ወለላው ከማይካድራ ከተማ በቅርብ ርቀት ላይ ስምሪት በተሰጣቸው የጸጥታ አካላት በቁጥጥር ስር ውሏል ብለዋል።

የጸጥታ ሠራዊቱ እጹን ሲያዘዋውሩ የነበሩ አካላትን በቁጥጥር ስር ለማዋል እየሠራ መኾኑንም አስረድተዋል።

የጸጥታ ሠራዊቱ የጥምቀትን በዓል በሰላም እንዲከበር ከተሰጠው ስምሪት ባሻገር፤ በዓሉን ተገን አድርገው ሊፈጸሙ የሚችሉ ሕገ ወጥ ድርጊቶችን እና ወንጀሎችን በመከታተል፣ በማምከን እና በቁጥጥር ስር በማዋል ረገድ ከፍተኛ ተግባር መፈጸሙን አንስተዋል። የጥምቀት በዓልም በሰላም ተጠናቋል ብለዋል።

ጥምቀት ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሕዝብ የሚሳተፍበት የአደባባይ በዓል በመኾኑ የዞኑ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ እና የጸጥታ መዋቅሩ በመቀናጀት ከውስጥም ከውጭም ሊፈጠሩ የሚችሉ የጸጥታ ስጋቶችን በመቆጣጠር በዓሉ በሰላም እንዲከበር ተደርጓል ነው ያሉት።

የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞንን ሰላም ለማጽናት ሁሉም የጸጥታ መዋቅር በቅንጅት እየሠራ ሲኾን ኅብረተሰቡ አጋርነቱን አጠናክሮ እንዲቀጥል መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

ዘጋቢ:- አምሳሉ አሞኘ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበጣና ዙሪያ የሚገኙ ቅርሶችን ተጨማሪ የቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ እየተሠራ ነው።
Next article“በሙሽርነቷ ያለች፤ በክብሯ የኖረች”