
ባሕር ዳር፡ ጥር 12/2018 (አሚሚኮ) የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ባሕል፣ ቱሪዝም እና ስፖርት መምሪያ የጥምቀት በዓል እና አበርክቶውን አስመልክቶ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይት አካሂዷል።
በመርሐ ግብሩ ላይ የተለያዩ አድባራት መሪዎች፣ የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ምሁራን እና የማኅበረ ቅዱሳን አባላት ተገኝተዋል።
የሐዲስ ኪዳን መምህር የኾኑት ኃይለማርያም ዘውዱ የጥምቀት በዓል ሲከበር ነገረ ድኅነታዊ መሠረቱ ላይ ትኩረት መሥጠት እንደሚገባ አሳስበዋል። በታላላቅ ከተሞች በቂ ትምህርተ ወንጌል መስጠት እና መንፈሳዊነቱ ላይ ማተኮር እንደሚገባም አንስተዋል።
ሌላኛው ጥናት ያቀረቡት የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የታሪክ እና ቅርስ አሥተዳደር ክፍል መምህር እና ተመራማሪ
አሥራት አርዓያ (ዶ.ር) የጥምቀት ክብረ በዓል ከሃይማኖታዊ ፋይዳው ባለፈ ማኅበራዊ ትስስር በመፍጠር እና የጋራ አሴቶችን በማጠናከር ለሀገር ግንባታ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ የሚገኝ እሴት መኾኑን ገልጸዋል። በተለይም ደግሞ በሕዝብ ለሕዝብ ግንኙኘት ማኅበራዊ ተግባቦት እና መቀራረብን የሚፈጥር የዓደባባይ በዓል መኾኑን ገልጸዋል።
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ባሕል፣ ቱሪዝም እና ስፖርት መምሪያ ኀላፊ ጋሻው እንዳለው እንደገለጹት የጥምቀት በዓል ከሃይማኖታዊ እሴትነቱ ባለፈ ማኅበራዊ መሥተጋብርን በማጠናከር እና የሀገርን ገጽታ በማጠናከር ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ ይገኛል።
ይህንን ሃይማኖታዊ እሴት ይበልጥ ለማሳደግ መምሪያው ባለፉት ዓመታት ከባሕር ዳር ሀገረ ስብከት ጋር በመቀናጀት እየሠራ መኾኑን ገልጸዋል።
በተለይም ደግሞ “ጥርን በባሕር ዳር” መርሐ ግብር ከተጀመረ ጀምሮ በከተማዋ የተለያዩ ሁነቶችን ከማዘጋጀት ባለፈ የከተራ፣ የጥምቀት፣ የቃና ዘገሊላ፣ የሩፋኤል፣ የሰባሩ ጊዮርጊስ እና የአሥተርዮ ማርያምን በዓላት በማክበር ከተማዋን የቱሪዝም መዳረሻ የማድረግ ሥራ መሠራቱን ገልጸዋል። በተለይም ደግሞ በዓላቱ በዓባይ እና ጣና ዙሪያ የሚከበሩ በመኾናቸው ለከተማዋ የተለየ ድምቀት ሰጥተዋል።
በጣና እና ዓባይ ዙሪያ የሚገኙ ቅርሶችንም በማልማት እና በማስተዋወቅ የቱሪዝም መዳረሻዎችን የማስፋት ሥራ እየተሠራ መኾኑንም ገልጸዋል።
ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
