
ባሕር ዳር፡ ጥር 12/2018ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያን ጨምሮ በተለያዩ የዓለም ሀገራት የሚገኙ የክርስትና እምነት ተከታዮች ኢየሱስ ክርስቶስ በፈለገ ዮርዳኖስ የተጠመቀበትን ዕለት በማሰብ የጥምቀት በዓልን በተለያዩ ሥነ ሥርዓቶች ያከብሩታል።
በዓሉ ተመሳሳይ ሃይማኖታዊ መሠረት ያለው ቢኾንም አከባበሩ ከሀገር ሀገር የተለያየ እና በዓለም ዙሪያ የሚገኙ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ምዕመናንን በአንድነት የሚያስተሳስር ታላቅ መንፈሳዊ እና ባሕላዊ እሴት ኾኖ ቀጥሏል።
በኢትዮጵያ እና በኤርትራ በዓሉ ከጥር 10 ጀምሮ እስከ ጥር 12 (ከከተራ እስከ ቃና ዘገሊላ) በተመሳሳይ ሃይማኖታዊ ሥርዓት ተከብሮ ይውላል። ሩሲያ፣ ዩክሬን እና ጆርዳን ደግሞ ጥር 11 ብቻ ከሚያከብሩት መካከል ለአብነት ተጠቃሽ ናቸው።
በኢትዮጵያ እና ኤርትራ በገጠርም ኾነ በከተማ በሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት ከዋዜማው ጀምሮ ታቦታቱ በምስጋና ታጅበው ከመንበረ ክብራቸው በመነሳት ወደ ባሕረ ጥምቀት ወርደው ያድራሉ። ሌሊቱን ሙሉ ከሚደረገው ማህሌታዊ ዝማሬ ባሻገር እንደየ አካባቢው ባሕል ደግሞ የተለያዩ ሥነ ሥርዓቶች እየተከናወኑ በማግስቱ ጠዋት የጠመቃ ሥርዓቱ ተከናውኖ ታቦታቱን በማጀብ ወደ መንበረ ክብራቸው በመመለስ ይከበራል።
ጎን ለጎንም ከሃይማኖታዊ ሥርዓቱ ውጭ ቢኾንም የተለያዩ ባሕላዊ ሁነቶች ይከወናሉ። የበዓሉ ተሳታፊዎችም ነጭ ባሕላዊ የሀበሻ ልብስ በመልበስ ይሳተፋሉ።
በሁለቱ ሀገራት የሚከበረው የጥምቀት በዓል ከሃይማኖታዊ ይዘቱ ባለፈ በሺዎች የሚቆጠሩ የውጭ ሀገር ጎብኝዎችን የሚስብ ታላቅ የቱሪስት መዳረሻ ኾኗል። ይህ በዓል በኢትዮጵያ ያለው አከባበር በ2012 ዓ.ም በዩኔስኮ የማይታይ የዓለም ቅርስ ኾኖ መመዝገቡም ይታወሳል።
በሩሲያ እና በሌሎች የምሥራቅ አውሮፓ ሀገራት ደግሞ ኢየሱስ ክርስቶስ በዮርዳኖስ ወንዝ መጠመቁን እና ሥላሴዎችን ለማስታወስ በበረዶ ውኃ ውስጥ ራሳቸውን ሦስት ጊዜ በመንከር ጥምቀትን ያከብራሉ።
በእነዚህ ሀገራት የሚገኙ ኦርቶዶክሳዊያን ይህን የሚያደርጉት ቅዱስ ውኃው ከኃጥያታቸው እንደሚያነጻቸው በማመንም ጭምር ነው።
ዩክሬናውያንም በረዶን በመስቀል ቅርጽ ከቆረጡ በኋላ በጥልቅ ቀዝቃዛ ውኃ ውስጥ ራሳቸውን በመንከር የጥምቀት በዓልን ያከብራሉ።
በቱርክየ፣ በቦስኒያ እና ሄርዞጎቪኒያ የሚገኙት የእምነቱ ተከታዮች ደግሞ በቄሶች ወደ ውኃ የተጣለውን የእንጨት መስቀል ለመያዝ የዋና ፉክክር በማድረግ ያከብራሉ።
በዋና ውድድሩ መስቀሉን መያዝ የቻለ ሰው ዓመቱን በሙሉ የተባረከ ይኾናል ብለውም ያምናሉ። በተለይም ቱርክየዎች ይህ ሥርዓት ጤና እና ብልጽግናን ያመጣል የሚል እምነትም አላቸው። በዚህ ሥርዓት መሳተፍ የክብር እና ጥንካሬ ምልክት ተደርጎም ይቆጠራል።
በሜክሲኮ ያለው የጥምቀት በዓል አከባበር ልማድ ደግሞ የተለየ ነው። በቀለበት ቅርፅ በውስጡ በማይታይ መልኩ የኢየሱስ ክርስቶስ ምስል የተሠራበት ዘውድ ያጠለቀ የሚመስል ጣፋጭ ኬክ በመመገብ በዓሉን ማክበር የተለመደ ነው።
በኬኩ መሐል በድብቅ የተሠራው የኢየሱስ ክስርቶስ ምስል ሕጻኑ ኢየሱስ ከንጉሥ ሄሮዶስ ለመሰወር የተደረገውን ሁነት ለማስታወስ ሲባል የሚደረግ መኾኑን ቢቢሲ ላይ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
አሚኮ ዲጅታል ሚዲያም ከብዙ በጥቂቱ ለትውስታ መረጃውን አጋራችሁ። ሰላም!
ዘጋቢ ፦ ሮዛ የሻነህ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
