
ባሕር ዳር፡ ጥር 10/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የጥምቀት በዓል አከባበር ሃይማኖታዊ ብቻ ሳይኾን ባሕላዊ ይዘትም ያለው ነው።
ጥምቀትን ከሚያደምቁ ባሕላዊ ክዋኔዎች መካከል ደግሞ በበዓሉ ተሳታፊዎች የሚቀርቡ ባሕላዊ ዜማዎች እና እስክስታ ይገኙበታል።
የ63 ዓመት የዕድሜ ባለጸጋ የኾኑት የአዴት ከተማ ነዋሪው አቶ ክንዱ ባየ ከልጅነታቸው ጀምሮ በጥምቀት በዓል ባሕላዊ ዜማዎችን በማዜም እና እስክስታ በመምታት ይታወቃሉ። ባሕል እና ትውፊት ለቀጣይ ትውልድ እንዲተላለፍ ካላቸው ፍላጎት አንጻርም ዕድሜ ሳይገድባቸው ዛሬም በጥምቀት በዓል ከማዜም እና ከማስጨፈር እንዳልተቆጠቡ አጫውተውናል።
በጥምቀት ያፈሯቸው ወዳጅ ዘመዶችም ጨፍረው እና በጆሮ ገብ ድምጻቸው አዚመው እንዲድሯቸው ከመጠየቅ አልተገቱም። እርሳቸውም ወዳጅን ማክበር ያውቁበታልና አያሳፍሯቸውም።
እኔም የኋላ ታሪክን ከዚህ ዘመን ጋር አጋምደው እንዲያጫውቱኝ የእጅ ስልኬን አንስቸ ሳጮህ ልጄ አንድ ወዳጄ ጨፍረህ ካልዳርከኝ ብሎ ሰርግ ላይ ኾኘ በማለት ነበር በፈገግታ የታጀበ ቀጠሮ የሰጡኝ።
አቶ ክንዱ ለሚኖሩበት አደት ከተማ የጥምቀት ባሕላዊ ዜማ አቀንቃኝ እና የቀደመው ትውፊት ምልክት ናቸው። የብዙ ሰርጎች ግርማ ሞገስ ጭምርም እንድሁ።
በማኅበረሰቡ ተወዳጅ እና አክብሮት የሚሰጣቸውም ናቸው። ማኅበረሰቡ ያለውን ፍቅር ለመግለጽ ሸጋው ክንዱ ባየ ሲል ቅጽል ስም አውጥቶላቸዋል። ዜማ ብቻ ሳይኾን ጨዋታ አዋቂም ናቸውና ድንገት ያገኛቸው ሁሉ የከበረ ሰላምታ ችሮ አብሯቸው ጊዜ ለማሳለፍ እጅ ከመዘርጋት አይቆጠብም። በቃ ጥርስ አያስከድኑም የሚባሉ አይነት ሰው ናቸው።
ለጥምቀት ያልኾነ ቀሚስ ይበጣጠስ እንደሚባለው ለጥምቀት ያልኾነ ጨዋታ እና ጭፈራ የሚሉ አይነት ሰው ናቸው አቶ ክንዱ።
በሕይዎት እያለሁ ለጥምቀት ደከመኝ አልልም፤ ጥምቀት ጥምቀት ነው እርጅና አይገድበውም ያሉም ናቸው። ብልህም ናቸውና በቃል ያለ ይረሳል በጽሑፍ ያለ ይወረሳል እንዲሉ አበው የግጥም መድብልም ደርሰዋል። በጨዋታችን መካከል ለጥምቀት አዲስ ባሕላዊ ልብስ አዘጋጅተው ለቃላዊ ግጥም እና ዜማ ዝግጅት ሲያደረጉ እንደነበርም አንስተውልኛል።
ወጣቶችም ወደ እርሳቸው መኖሪያ አካባቢ በማቅናት ስለዘንድሮው የጥምቀት በዓል ምክር ጠይቀዋቸዋል። የሚገጥሟቸው ግጥሞች እና የሚያዜሟቸው ዜማዎች ሃይማኖታዊ የበዓል አከባበሩን ከማጀብ አልፈው ማኅበረሰብን የሚያዋድዱ፤ የሚያፋቅሩ፣ የጋራ የሚያደርጉ፤ ልክ ያልኾነ ነገርን የሚገስጹ፤ ሰላምን የሚሰብኩ፤ ነፍስን ከስጋ የሚያስታርቁ፤ አዕምሮ ቆም ብሎ እንዲያስብ የሚያደርጉ እና ለልብ እረፍት የሚሰጡ በባሕል የተዋዙ ናቸው።
ሸንኮራ አገዳ ይዟል በእጁ(2)
ጌታየ መድህኔ ለወዳጁ።
እጣን እጣን ይሸታል መሬቱ (2)
ጌታየ መድህኔ የወረደበቱ።
አንተን አምኘ ምን ኾኘ(2)
መድህኔን አምኘ ምን ኾኘ
ጌታየን አምኘ ምን ኾኘ
እናቴን አምኘ ምን ኾኘ(2)
አድነኝ እና ልንገር ወሬ(2)
ሂጀ ተሻግሬ በሸዋ በትግሬ።
አድነኝ እና ልደግስ (2)
ስምክን እያነሳሁ ለዓለም ላድርስ።
እረ ማን አሉህ ስምህን(2)
የሰማዩን ንጉስ አንተን ፈጣሪን።
እያሉ በዜማ ያወድሳሉ።
በግጥም እና ዜማቸው ተመስጨ ትንፋሼን ዋጥ አድርጌ እንደልጅነቴ አኩኩሉ ጨዋታ እርሳቸውን በጉጉት አደመጥኩ። እርሳቸውም ቀጠሉና ጥርስ አያስከድኑም የተባለውን ጨዋታቸው አምጥተው እንደ ጅረት አወረዱታ።
የጥምቀት የልደት ያልታጨች ቆንጆ
ቁማ ትቀራለች እንደዘላን ጎጆ።
ሲሉ ቀልድ መሳይ ተረቡ። ወጣቶች ውኃ አጣጫቸውን የጥምቀት በዓልን አጋጣሚ ተጠቅመው ቆም ብለው እንዲያስቡ ማድረጊያ መኾኑ ግልጽ ነው።
በጨዋታችን መካከል አሁን ላይ ከቀደመው ባሕላዊ ክዋኔ እና ትውፊት ጋር የማይገናኙ ዜማዎች ሲዜሙ መስማታቸውን ታዝበዋል። ይህም የቀደመውን እሴት ስለሚጻረር ሊታረም እንደሚገባ ነው ያስገነዘቡት። ቆየት ያለውን ዘመን ባሕል እና እሴት አክባሪው አቶ ክንዱ ባየ መማር የባሕሪ ለውጥ ማምጣት ስለኾነ ሁሉም በየድረሻው ባሕላዊ ትውፊቱ እንዲቀጥል መክረዋል።
እርሳቸው የእርሳቸውን አርያ የሚከተሉ በርካታ ተተኪ ወጣቶችን አፍርተዋል፤ እያፈሩም ነው።
ወጣት አለማየሁ ሳህሉ እርሳቸውን በጥምቀት በዓል ሲያዜሙ እያደመጠ እስክስታ ሲመቱ እየተመለከተ ነው ያደገው። የተዘራች መልካም ዘር አብባ ፍሬ ትኾናለች እና በጥምቀት በዓል እና ሃይማኖታዊ የንግሥ በዓሎች ላይ ባሕላዊ ዜማዎችን ያዜማል። በጥምቀት ወቅት የሚያዜማቸው ግጥሞች በብዛት መንፈሳዊ ይዘት ያላቸው ናቸው። አልፎ አልፎ ግን ጨዋታው እንዲደራ፤ ውኃ አጣጭ መፈለግ ያሻው ውኃ አጣጩን በዐይኑ እንዲቃኝ ጠቆም የሚያደርጉ ግጥም እና ዜማንም ያወርዳል።
ያለው ባለው የሌለው ተውሶ በጥምቀት በዓል ደምቆ እና ተውቦ እንደሚውል ለመጠቆምም ግጥም መገጠሙ አይቀርም። በሌሎች ቀናቶች የማይሞቀው፤ የማይበርደው ሁሉ ለጥምቀት ባለው አቅም ሸክ ይላል። እንደ ወጣት አለማየሁ ያሉ የጥምቀት በዓል ገጣሚ እና አዚያሚዎች በአሽሙር ሸንቆጥ ማድረጋቸውን አይተውም።
ዛሬስ አመዶ ምን አይተሻል፣
ዛሬስ አመዶ ምን መስለሻል፣
የሰው ጥላ ተውሰሻል፣
የሰው ቀሚስ ተውሰሻል፣
የሰው ማሠሪያ ተውሰሻል (የፀጉር)።
እያለ ትናንትን ከዛሬ፤ ዛሬን ከነገ እያስማማ ታሪክ ነገራን ለቀጣዩ ትውልድ የቤት ሥራ እየሰጠ፤ ከእርሱ በዕድሜ ለሚያንሱ ታዳጊ ወጣቶች ሰብሰብ አድርጎ እንደሚያስጨፍርም አጫውቶናል።
ወጣቱ እንዲህ አይነት ዜማዎችን የማዜም ልምምዱ አንድ ባሕላዊ ነጠላ ዜማ ለህዝብ እንዲያደርስ አስችሎታል። አሁን ላይም ሌላ ነጠላ ዜማ እንዲሠራ ስንቅ አቀብሎታል።
አባቶች ትናንትን ለዛሬ ከእነ ትውፊቱ እንዳቀበሉን ዛሬን ለነገ እናቀብል እላለሁ።
መልካም የጥምቀት በዓል !
ዘጋቢ፦ ሮዛ የሻነህ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
