
ባሕር ዳር ፡ ጥር 12/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ጥምቀት በኅብረ ቀለማት ያሸበረቀ፤ ከሊቅ እስከ ደቂቅ የሚሳተፍበት ሃይማኖታዊ በዓል ነው። እንደሌሎቹ በዓላት በቤት ውስጥ የተገደበ ሳይኾን በአደባባይ የሚከበር ደማቅ በዓልም ነው።
ከሃይማኖታዊ ሥርዓቱ ባሻገር ባሕላዊ ወግ እና ሥርዓቶችን አጣምሮ ያቀፈ፤ ከከተራ አንስቶ እስከ ቃና ዘገሊላ ድረስ የተለያዩ ትዕይንቶች የሚስተናገዱበት ታላቅ በዓል ነው ጥምቀት።
ሃይማኖታዊ መሠረት ባይኖረውም ማኅበረሰቡ ከፈጠራቸው ትይንቶች መካከል ሎሚ ውርወራ አንዱ ነው ። ሎሚ የመልካም መዓዛ እና የፍቅር ስሜት መግለጫ ተደርጎ በማኅበረሰቡ ዘንድ የሚታወቅም ነው፡፡ ከመነገር አልፎም በሁነት ታጅቧል፤ ተዘፍኖለታል። በጥምቀት ሎሚ ውርወራ ተጫጭተው ለትዳር የበቁ፤ ወልደው የከበዱ ጥንዶችን ብዛት ቤቱ ይቁጠራቸው።
የ67 ዓመት የዕድሜ ባለጸጋ የኾኑ እና ስማቸውን መግለጽ ፈቃደኛ ያልኾኑት የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪ ባለታሪካችን እንደነገሩን ውኃ አጣጫቸው ጋር የተጣመሩት በጥምቀት ሃይማኖታዊ በዓል በወረወሯት ሎሚ ምክንያት እንደነበር አጫውተውናል።
በሎሚ ውርወራ በተመሠረተ ትዳር አንድ ወንድ እና ሦስት ሴት ልጆችን አፍርተዋል። ከአሚኮ ዲጅታል ሚዲያ ጋረ ቆይታ ያደረጉት እኒህ ሰው ፈጣሪ ይመሥገን ሁሉም ለቁም ነገር ደርሰውልኛል ሲሉ ነገሩን።
ወቅቱን ሲያስታውሱም እነዚህን ልጆች የሰጠች የትዳር አጋራቸው እርሳቸውን በ21 ዓመታቸው ቀልባቸውን ያዝ አድርጋ ሎሚ ያስወረወረቻቸው የትዳር አጋራቸው ፈቃደኛ ትኾናለች ብለው አስበው እንዳልነበር አስታውሰዋል።
በኢኮኖሚ ዝቅ ያለ ቤተሰብ ላይ ስለተወለዱም እርሷ ፈቃደኛ ብትኾን እንኳ ዘመዶቿ ላይኾኑ ይችላሉ የሚል ስጋትም ነበረባቸው።
ሎሚ ወርውሬ የቀሚሷን ጥለት ቀርጭፎት ሎሚው መሬት ላይ ሲወድቅ ሀፍረት በተሞላበት የተሸበበ ፈገግታ ወደ ጎን አሻግራ አይታ ስትቆም እኔ ጠጋ ብየ የወደቀውን ሎሚ አንስቸ በእጇ ሰጠኋት ብለው ፈገግ አሉ።
ዓይናቸው ያረፈባትን የትዳር አጋራቸው ባይለምዳትም ቀደም ሲል አይተዋት ያውቁ ነበር። ከእርሷ ጋር ተዋውቀው፤ አካባቢዋን እና የማን ልጅ እንደኾነች አጣርተው ከቆዩ ከሳምንት በኋላ ለቤተሰባቸው አሳውቀው እንድትታጭላቸው አደረጉ።
ከሦስት ጊዜ ምልልስ በኋላ ተፈቅዶላቸው ለሰርግ ዝግጅት ሲደረግ ቆይቶ በፋሲካ በዓል በደመቀ የገጠር ባሕላዊ ሠርግ ጋብቻ መስርተዋል።
አሁን ላይ የትዳር አጋራቸው በሕይወት ባይኖሩም ከእሷ ውጭ ምንም ሳያውቁ በልባቸው በተሞላ ጽኑ ፍቅር ያነገሷትን ሚስታቸውን እያስታወሱ ትዳር መስርታ እና ልጆች ወልዳ ከምትኖር ልጃቸው ጋር ኑሮን እያሳለፋ ይገኛሉ።
ታሪኩን ሲነግሩኝ ወደ ፈጣሪ ስንጠራ ምክንያት እንዳለ ባምንም በእንባ የታጀበውን አይናቸውን አይቸ ምናለ በቆዩላቸው ብየ ተመኘሁ።
ሀሳብ አጋሪያችን የ67 ዓመቱ አረጋዊ ሎሚ ውርወራ ብዙ ጥንዶችን ለማጣመር አንድ አጋጣሚ እና ትልቅ ትርጉም የነበረው ቢኾንም ዛሬ ላይ ባሉ ታዳጊዎች ዘንድ ግን እንደቀልድ መቆጠሩ እንዳሳዘናቸው ጠቅሰውልናል።
ባሕሉ እየጠፋም ይመስላል ሲሉ ትዝብታቸውን አጫውተውናል። በቀደመው ጊዜ ከሎሚ ውርወራ ጋር ተያይዞ ሲዜሙ ከነበሩ ዜማዎች መካከልም ቀጣዩን አሉኝ።
“ሎሚ ብወረውር ደረቷን መታሁት
አወይ ኩላሊቷን ልቧን ባገኘሁት።
ይኼው ደረትሽ ነው ያጣላኝ ሁሉን፤
እስቲ ሸፈን አርጊው ያጡት እንድኾን?
ሎሚ ጣሉባት በደረቷ
የጨዋ ዘር ነው መሠረቷ
አንቺዬ ሎሚ ነሽ ወይ
ላሽትሽ ወይ”
እያሉ ያዜሙ እንደነበር ገልጸውልኛል። የትናንት የሀገራችን በጎ ባሕሎች መጠበቅ እና ማስቀጠል ይገባል፤ እንደቀልድ አትዩአቸው ሲሉም መክረዋል።
መልካም የጥምቀት በዓል!
ዘጋቢ፦ ሮዛ የሻነህ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
