ከ150 በላይ ድርጅቶች ፌስቡክ የጥላቻ ንግግርን አላስቆመም በሚል እየተቃወሙት ነው፡፡

254

ባሕር ዳር፡ ሰኔ 22/2012 ዓ.ም (አብመድ) ስታርባክስ፣ ኮካ ኮላ እና ሌሎችም የንግድ ድርጅቶች ምርታቸውን በማኅበራዊ ሚዲያ ማስተዋወቅ ሊያቆሙ መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡

ስታርባክስ የጥላቻ ንግግርን ለመቃወም ሲል በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ምርቱን ማስተዋወቁን እንደሚያቆም አስታውቋል፡፡

የአሜሪካው ግዙፉ የቡና አቅራቢ ምርቶቹን በማኅበራዊ ሚዲያ ላለማስተዋወቅ የወሰነው የማኅበራዊ ሚዲያ ዘርፎች የጥላቻ ንግግርን እንዲያወግዙ እና እንዳይፈቅዱ የሚያደርግ ጫና ለመፍጠር መሆኑን አስታውቋል፡፡ በመሆኑም በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በክፍያ ምርቶቹን ማስተዋወቁን እንደሚያቆም ነው የገለጸው፡፡

ዘረኝነትን መከላከልና ማስቆም በሚቻልባቸው መንገዶች ላይ ከመገናኛ ብዙኃን ባለቤቶችና ከሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ጋር እየተነጋገረ መሆኑንም ስታርባክስ አስታውቋል፡፡

ኮካ ኮላም ይህን ዓላማ በመደገፍ ለሚቀጥሉት 30 ቀናት በማኅበራዊ ሚዲያ የሚያሠራቸውን የምርቶቹን ማስታወቂያዎች እንደሚያቋርጥ መግለጹ ይታዎሳል፡፡ የማኅበራዊ ሚዲያ ዘርፎች የጥላቻ ንግግር ማራመጃ መድረኮች እየሆኑ መምጣታቸው እየታወቀ ድርጊቱን ለማስቆም ያሳዩትን ቸልተኝነት በመቃዎም ሌሎች ዓለም አቀፍ የንግድ ተቋማትም ዘመቻውን እየተቀላቀሉ እንደሚገኙ ቢቢሲ ዘግቧል፡፡

“ከጥላቻ ንግግር የሚገኝ ትርፍ ይቁም” በሚል ሀሳብ ማኅበራዊ ሚዲያን የመቃወም እንቅስቃሴም ተጀምሯል፡፡ የዘመቻው አስተባባሪዎችም ፌስቡክ የጥላቻ ንግግሮችና ሐሰተኛ መረጃዎች እንዳይሰራጩ ኃላፊነቱን እንዳልተወጣ በመግለጽ እየተቃወሙት ነው፡፡ ከ150 በላይ ድርጅቶች የዚህን ዘመቻ ሀሳብ በመደገፍ ምርታቸውን ማስተዋወቅ ማቆማቸው ተዘግቧል፡፡

የፌስቡክ መሥራች ማርክ ዙከርበርግ በበኩላቸው ከዘረኝነት፣ ከጥላቻ፣ ከስደተኝነት እና ከሌሎችም ጋር የተያያዙ ማስታወቂያዎች በፌስቡክ በኩል እንዳይስተናገዱ እንደሚያደርጉ አስታውቀዋል፡፡

በአስማማው በቀለ

Previous articleበኮሮናቫይረስ ምክንያት የሟቾች ቁጥር ከግማሽ ሚሊዮን አለፈ፡፡
Next articleየሕዳሴ ግድቡ በዓመታዊ የውሃ ፍሰት ላይ ምንም ተጽእኖ እንደማይኖረው የቀድሞው የሱዳን የውኃ እና መስኖ ሚኒስትር አስገነዘቡ፡፡