
ገንዳ ውኃ: ጥር 11/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የጥምቀት በዓል ሃይማኖታዊ ሥርዓቱን ጠብቆ በምዕራብ ጎንደር ዞን ገንዳ ውኃ ከተማ በድምቀት እየተከበረ ነው።
የዚህ ዓመት የጥምቀት በዓል የደመቀ እንደኾነ የበዓሉ ታዳሚዎች ተናግረዋል። የጥምቀት በዓል አስተምህሮ ትህትና እና ዝቅ ብሎ ማገልገል መኾኑንም ገልጸዋል።
የምዕራብ ጎንደር ዞን ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ብጹዕ አቡነ ሰላማ በባሕረ ጥምቀቱ ተገኝተው ቃለ ቡራኬ ሰጥተዋል።
ኢየሱስ ክርስቶስ ከሰማይ የወረደው እና በዮርዳኖስ ወንዝ የተጠመቀው እሱ ያጣው ክብር ኖሮ ሳይኾን ምዕመኑ የጎደለውን መንፈሳዊ ሀብት ሊሞላ ነው ብለዋል።
ኢየሱስ ክርስቶስ ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ ወንዝ ወርዶ ኃጥያት ሳይኖርበት ስለሰዎች በደል በአገልጋዩ በዮሐንስ እጅ መጠመቁን የምናስተምርበት ቀን ነው ብለዋል።
ክርስቶስ ከሰማይ የወረደው፤ ከሰው የተወለደው፤ በዮርዳኖስ የተጠመቀው፤ የተሰቀለው፣ የሞተው እና በሦስተኛው ቀን የተነሳው፤ በመጨረሻም ያረገው የጠፋውን የሰውን ልጅ ለመፈለግ እንደኾነ ብጹዕነታቸው አስተምረዋል።
ሕዝበ ምዕመኑ እርስ በእርስ በበጎ ተግባር በመፈላለግ፣ በመደጋገፍ፣ በመተሳሰብ እና በመረዳዳት በዓሉን ሊያከብር ይገባል ነው ያሉት።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
