
ፍኖተ ሰላም: ጥር 11/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የኢየሱስ ክርስቶስ የጥምቀት በዓል በተለያዩ ሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓቶች በፍኖተ ሰላም ከተማ በድምቀት እየተከበረ ይገኛል።
በበዓሉ የምዕራብ ጎጃም ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ብጹዕ አቡነ ዘካርያስ ለምዕመኑ ትምህርት ሰጥተዋል። በትምህርታቸውም ኢየሱስ ክርስቶስ በተጠመቀ ጊዜ የተዘጋው ሰማይ ተከፈተ በምድር ሁሉ ደስታ ኾነ ብለዋል።
“በጥምቀቱ የተራራቁት ተቀራረቡ፤ የተጣሉት ታረቁም” ነው ያሉት።
የሰው ልጅ በሠራው ኃጥያት ከፈጣሪ ተጣልቶ የነበረው በጥምቀት ታረቀ ብለዋል ብጹዕ አቡነ ዘካርያስ። የተጣሉት በመታረቃቸው ጥምቀት የሰላም ምልክት መኾኑንም ጠቁመዋል። ሁሉም የሰላምን መንገድ መከተል እና መስበክ ይጠበቅበታል ነው ያሉት።
በበዓሉ የመረዳዳት እና የመቻቻል ባሕላችንን በማጎልበት ከፈጣሪ የነፍስ ዋጋ ማግኘት ይገባልም ብለዋል።
የፍኖተ ሰላም ከተማ ምክትል ከንቲባ ጊዜው ደግአረገ ከተማው ባለፉት ሁለት ዓመታት ከገጠመው የጸጥታ ችግር ለመውጣት ከኅብረተሰቡ ጋር በመቀናጀት ወደ ተሻለ ሰላም ጉዞ ላይ ነው ብለዋል።
ልማትን ለማምጣት ሰላም ወሳኝ መኾኑን የገለጹት ምክትል ከንቲባው በከተማው እየተከናወኑ ያሉ የልማት ሥራዎችን ለማከናወን ኅብረተሰቡ እገዛ ማድረግ እንዳለበት አንስተዋል።
የጥምቀት ሥነ ሥርዓቱ ከተጠናቀቀ በኋላ ታቦታት በምዕመናን ታጅበው ወደ አድባራት እና ገዳማት እየተመለሱ ይገኛሉ።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
