
ባሕር ዳር፡ ሰኔ 22/2012 ዓ.ም (አብመድ) በዓለማችን በኮሮናቫይረስ ምክንያት ሕይዎታቸውን ያጡት ሰዎች ከግማሽ ሚሊዮን ማለፉ ታውቋል፡፡
ይህ ዜና እስከተጠናቀረበት ሰዓት ድረስ በመላው ዓለም በኮሮናቫይረስ ሕይወታቸውን ያጡት ሰዎች ቁጥር 504 ሺህ 478 መድረሱን የጆን ሆፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ መረጃ ያመላክታል፡፡
በቫይረሱ የተያዙት ደግሞ 10 ሚሊዮን 249 ሺህ 470 ደርሰዋል፤ 5 ሚሊዮን 556 ሺህ 644 ሰዎች ማገገማቸውም ታውቋል፡፡
በአፍሪካ ደግሞ 385 ሺህ 219 ሰዎች ናቸው በኮሮናቫይረስ የተያዙት፡፡ ከእነዚህ መካከል 9 ሺህ 698 ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል፤ 185 ሺህ 243 ሰዎች አገግመዋል፡፡
በኢትዮጵያም ቫይረሱ በምርመራ የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥር 5 ሺህ 689 ደርሷል፤ በሀገሪቱ እስከዛሬ በቫይረሱ ምክንያት ሕይወታቸው ያለፈ ሰዎች ቁጥር 98 ደርሷል፤ 2ሺህ 132 ሰዎች ደግሞ አገግመዋል፡፡
የቫይረሱ ስርጭት በአሳሳቢ ደረጃ መስፋፋቱ እንደቀጠለ መሆኑን ተከትሎ የዓለም ጤና ድርጅት አሁንም መዘናጋት እንደማይገባ እያሳሰበ ነው፡፡ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ የዓለምን ግድየለሽነት ያሳዬ መሆኑን በማመላከትም ሀገራት መከላከሉ ላይ ትኩረት አድርገው እንዲሠሩ ማሳሰቡ ይታወሳል፡፡