
ሁመራ፡ ጥር 11/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን የጥምቀት በዓል በሰቲት ሁመራ ከተማ የተከዜ ወንዝ ዳርቻ በድምቀት እየተከበረ ነው።
“ጥምቀት የአንድነት እና የነጻነት በዓል ነው” ያሉት የዞኑ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አሥኪያጅ መጋቤ ሐዲስ መምህር ዜናዊ አሸተ ናቸው። “የጥምቀት በዓል በክርስቶስ ክርስቲያን የተባልንበት ልዩ በዓላችን ነውም” ብለዋል። ክርስቲያን ለመባላችን መነሻው ጥምቀት መኾኑንም አስረድተዋል። ይሄም ከአምላካችን ከእግዚአብሔር ጋር የምንገናኝበት ምስጢር እንደኾነ ነው የገለጹት።
በመኾኑም ሕዝበ ክርስቲያኑ ጥምቀትን ጨምሮ ሌሎች በዓላትን ሲያከብር እርስ በእርስ በመተጋገዝ እና ካለው ላይ በመካፈል ሊኾን እንደሚገባም አሳስበዋል።
የዞኑ ሕዝብ እና አሥተዳደሩ በቅንጅት የአካባቢውን ሰላም ለመጠበቅ በቁርጠኝነት በመሥራቱ የጥምቀት በዓልን በደመቀ ሁኔታ ማክበር መቻሉን የተናገሩት ደግሞ የዞኑ ምክትል አሥተዳዳሪ እና የሰላም እና ጸጥታ መምሪያ ኀላፊ ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ ናቸው።
ሰላም ሲኖር ልማት እና እድገት አለ ያሉት ኮሎኔል ደመቀ ሰላም ከሌለ ሁሉም ነገር እንደማይኖር አንስተዋል። የሰላምን ወሳኝነት በመገንዘብ ሁሉም የማኅበረሰብ ክፍል ለሰላም በትብብር ሊሠራ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
መተባበር እና መተጋገዝ ውጤታማ እንደሚያደርግ ያነሱት ኮሎኔል ደመቀ የዞኑ ወጣቶች አካባቢያቸውን በንቃት ለመጠበቅ እና ለጸጥታ አካላት ድጋፍ በመኾን እያሳዩት ያለውን ቁርጠኝነት ሊያስቀጥሉት እንደሚገባ አሳስበዋል።
የተገኘውን ነጻነተ ተከትሎ ከ27 ዓመታት በኋላ የጥምቀትን በዓል ለሦስተኛ ጊዜ በተከዜ ወንዝ ዳርቻ እያከበሩ በመኾናቸው ደስተኛ መኾናቸውን በቦታው ያነጋገርናቸው የበዓሉ ተሳታፊዎች ገልጸውልናል።
ባለፉት ዓመታት የጥምቀት አከባበር ከተከዜ ወንዝ ዳርቻ ሸሽቶ ሌላ ቅርጽ ይዞ ይከበር እንደነበር አንስተው ዛሬ ላይ ጥንት አባቶቻችን ያከብሩበት ወደነበረው ቦታ ተመለሶ መከበሩ አስደሳች ነው ብለዋል።
ሕዝበ ክርስቲያኑም የጥምቀትን በዓል በነጻነት እና በፍቅር እያከበረ ሲኾን በጎንደር አማራ ባሕል፣ ወግ እና አለባበስ በዓሉን እያከበርን ነው ብለዋል።
ዘጋቢ:- አምሳሉ አሞኘ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
