ጥምቀት ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰው ልጆች ትህትና እና ፍቅርን በተግባር ያሳየበት ቀን ነው።

2

ደባርቅ: ጥር 11/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ ትልቅ ትርጉም ያለው የጥምቀት በዓል በሰሜን ጎንደር ዞን ደባርቅ ከተማ በድምቀት እየተከበረ ነው።

 

በዓሉ ሃይማኖታዊ፣ ባሕላዊ እና ማኅበራዊ እሴቱን ጠብቆ በተለያዩ ክዋኔዎች የሃይማኖት አባቶች እና የእምነቱ ተከታይ ምዕምናን በተገኙበት ነው እየተከናወነ ያለው።

 

የሰሜን ጎንደር ዞን ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አሥኪያጅ መልአከ ኃይል አስምሮ ዋካ የጥምቀት በዓል “ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰው ልጆች ትህትና እና ፍቅርን በተግባር ያሳየበት ቀን ነው” ብለዋል።

 

ምዕምናንም ይሄን ሥርዓት አብነት በማድረግ እርስ በእርስ በመረዳዳት እና በመከባበር ይሄን ቀን አስበውት ሊውሉ እንደሚገባ መልዕክት አስተላልፈዋል።

 

የደባርቅ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጌትነት ጸጋዬ የጥምቀት በዓል ከሃይማኖታዊ ፋይዳው በተጨማሪ ማኅበራዊ እና ባሕላዊ ዕሴቶች ጎልተው የሚታዩበት፤ ሀገራዊ ገጽታ የሚገነባበት በዓል ነው ብለዋል።

 

ሀገራችን ኢትዮጵያ በቱሪዝም ዘርፉ የተሻለ ተጠቃሚ እንድትኾን እንደ ጥምቀት ዓይነት የአደባባይ በዓላትን ይዘታቸውን ጠብቆ ማክበር ይገባዋል ነው ያሉት።

 

የበዓሉ ተሳታፊዎችም በበኩላቸው የጥምቀት በዓል ሃይማኖታዊ እና ባሕላዊ ገጽታው የጎላ የአደባባይ በዓል በመኾኑ በበዓሉ መታደማቸው የተለየ ደስታን እንደፈጠረላቸው ተናግረዋል። በዓሉ እሴቱን ጠብቆ በሰላም መከበሩንም ገልጸዋል።

 

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

👇👇👇

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

 

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ምዕመኑ የክርስቶስን መንገድ መከተል እና ትሕትናን መላበስ ይጠበቅበታል” ብጹዕ አቡነ ቶማስ
Next articleየጥምቀት በዓል በክርስቶስ ክርስቲያን የተባልንበት ልዩ በዓላችን ነው”