“ምዕመኑ የክርስቶስን መንገድ መከተል እና ትሕትናን መላበስ ይጠበቅበታል” ብጹዕ አቡነ ቶማስ

3

ደብረ ማርቆስ: ጥር 11/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የኢየሱስ ክርስቶስ የጥምቀት በዓል ሃይማኖታዊ ሥርዓቱን ጠብቆ በደብረ ማርቆስ ከተማ እየተከበረ ነው።

 

የምሥራቅ ጎጃም፣ የአዊ እና የመተከል አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እና የቅዱስ ሲኖዶሰ አባል ብጹዕ አቡነ ቶማስ የኢየሱስ ክርስቶስ መጠመቅ ፍቅርን፣ ሰላምን እና መተሳሰብን የሚያስተምረን መኾኑን በአስተምህሮታቸው አስገንዝበዋል።

 

የኢየሱስ ክርስቶስ በዮሐንስ እጅ በዮርዳኖስ ወንዝ መጠመቅ መታዘዝን፣ ትሕትናን፣ ፍቅርን እና መተሳሰብን ለሰው ልጆች ሁሉ የሚያስተምረን ነው ብለዋል።

 

የምሥራቅ ጎጃም ሀገረ ስብከት የወንጌል ክፍል ኀላፊ ሊቀ ሕሩያን መምህር ባሕረ ጥበብ አያሌው ሰላም ለሁሉም ፍጡር አስፈላጊ እንደኾነ ተናግረዋል። ሰላምን መሻት ከሁሉም አካል ይጠበቃልም ብለዋል።

 

ፈጣሪ የሰላም አምላክ ነው፤ ቤተክርስቲያን የሰላም ምሳሌ ናት፤ ዛሬም ኾነ ነገ ሰላምን ታስተምራለች፤ ምዕመኑ ለሰላም እና ለፍቅር በጸሎቱ መጽናት አለበት ነው ያሉት።

 

የጥምቀት በዓል የኢየሱስ ክርስቶስ በዮሐንስ መጠመቅን የምናስብበት፤ ማኅበራዊ ትስስራችንን የምናይበት፤ አንድነታችንን የምንገልጽበት፤ የምንማርበት ነው ያሉት ደግሞ የደብረ ማርቆስ ከተማ የጥምቀት ታዳሚዎች ናቸው።

 

ጥምቀቱ ሃይማኖታዊ እሴቱ ብቻ ሳይኾን ማኅበራዊ መተሳሰራችንን የምናጠናክርበት፤ ደምቀን እና ንጹሕ ኾነን የምናከብረው የአደባባይ በዓል ነው ብለዋል።

 

ወጣቶች ከከተራ በዓል ቀደም ብሎ የመንገድ እና የታቦታት ማረፊያዎችን ማስዋብ፤ የትራፊክ ፍሰትን ማስተካከል፤ የአካባቢ ጽዳት እና ሌሎችንም የበጎ ፈቃድ ሥራዎችን እየሠሩ በዓሉን እያሳለፉ ይገኛሉ።

 

ወጣቶች ይህን ልምድ ሁሌም ማጠንከር እና ማሳደግ ይገባቸዋል ብለዋል።

 

የከተማ አሥተዳደሩም በዓሉ በሰላም እንዲከበር የጸጥታ ሥራውን ከመቸውም ጊዜ በበለጠ ሢሠራ ቆይቷል ነው ያሉት።

 

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

👇👇👇

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

 

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleጥምቀት በአብሮነት ምልክቷ ከሚሴ ከተማ
Next articleጥምቀት ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰው ልጆች ትህትና እና ፍቅርን በተግባር ያሳየበት ቀን ነው።