”ልብስን ሳይኾን ልብን ንጹሕ ማድረግ ያስፈልጋል” ሊቀ ሊቃውንት ስምአኮነ መልዓክ

5

ባሕር ዳር: ጥር 11/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የጥምቀት በዓል ሥነ ሥርዓት በባሕር ዳር ከተማ ጣና ዳር ባሕረ ጥምቀት ላይ መካሄዱን እንደቀጠለ ነው።

 

በባሕር ዳር ሀገረ ስብከት የሊቃውንት ክፍል ኀላፊ እና የአራቱ ጉባኤያት የትርጓሜ መጻሕፍት የምሥክር መምህር ሊቀ ሊቃውንት ስምአኮነ መልዓክ ለምዕመኑ ትምሀርት ሰጥተዋል።

 

በኢየሱስ ክርስቶስ ጥምቀት ልጅነት፣ መንፈስ ቅዱስን እና ሰማያዊ ዜግነት ተሰጥቶናል ብለዋል።

 

ትዕቢት እና መታበይን መተው እንደሚገባም በሰጡት ትምህርት ላይ አንስተዋል።

 

ክርስቶስ ከደሃዎች ጋር ያለመለያየት ተጠምቆ ስላስተማረን ዛሬ በጥምቀት በዓል ሃብታም ድሃ ሳንለያይ በአንድ ላይ እናከብረዋለን ነው ያሉት።

 

በሌሎች መስተጋብሮቻችንም በሃብት እና በጉልበት ሳንለያይ ተባብሮ መኖር ይገባል ብለዋል ስምአኮነ መልዓክ።

 

“ልብስን ሳይኾን ልብን ማንጻት ከሰዎች ይጠበቃል” ነው ያሉት። ከሰለሞን ቤተ መቅደስን እና ከሌሎች የተሸላለሙ ድንኳኖች ይልቅ እግዚአብሔር የመረጠው ምድረ በዳውን ነው ብለዋል። እናም ከታይታ ንጻት ይልቅ የውስጥ እና የሕይወት ንጻትን ማስበለጥ አለብን ነው ያሉት።

 

ምድራዊ የነበርነው ሰማያዊ የኾነው ከሰው ብቻ ሳይኾን ከእግዚአብሔርም እንድንወለድ ያደረገን በጥምቀቱ ነው ብለዋል በአስተምህሯቸው።

 

ክርስቶስ በውኃ የተጠመቀው ኃጥያትን ሊሽር ነው ያሉት ሊቀ ሊቃውንት ስምአኮነ መልዓክ ሰዎች ከኃጥያት እንዲቆጠቡም አሳስበዋል።

 

እረፍት ቢሮ በመዝጋት ብቻ ሳይኾን የነፍስ እረፍትም ለማግኘት ከችግረኞች ጋር በመዋል፤ ከክፉ ሥራ በመታቀብ፤ መልካም ነገርን በማድረግ መኾኑንም ገልጸዋል።

 

ዘጋቢ፦ ዋሴ ባየ

 

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

👇👇👇

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

 

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleጥምቀት በገንዳ ውኃ ሃይማኖታዊ ሥርዓቱን ጠብቆ እየተከናወነ ነው።
Next articleጥምቀት በአብሮነት ምልክቷ ከሚሴ ከተማ