ለ 68 ቀናት በጽኑ ህመም ውስጥ የነበረው የኮሮና ቫይረስ ታማሚ አስደናቂ ፍጻሜ!

190

ባሕር ዳር፡ ሰኔ 21/2012 ዓ.ም (አብመድ) 68 ቀናትን በጽኑ ህመም ውስጥ ያሳለፈው እንግሊዛዊ አውሮፕላን አብራሪ በቬትናም ሆስፒታል ከኮሮና ጋር ያደረገው ተጋድሎ!

ስቴፈን ካሜሩን ትውልዱ በስኮትላንድ፣ በዜግነት ደግሞ እንግሊዛዊ ነው። አውሮፕላን አብራሪው ካሜሮን የኮሮና ወረርሽኝ በጀመረበት ሰሞን ነበር የተለመደ ስራውን እያከናወነ መጋቢት መጀመሪያ ላይ ከእንግሊዝ ወደ ቬትናም ያመራው፡፡ ቬትናም ሆ ቺ ሚንህ ከተማ እንደደረሰም ወደ አንድ የመዝናኛ ሥፍራ ያመራል። በቦታውም በርከት ያሉ ሰዎች ተሰባስበው መጠጥ እየተጎነጩ ነበር ይላል የቢቢሲ ዘገባ። ከምሽቱ 2፡00 አካባቢ በመጠጥ ቤቱ የተገኘው ስቴፈን ካሜሩን ጓኞቹ እንዲጠጣ ቢጋብዙትም ግብዣቸውን በአክብሮት ተቃወመ፡፡ እስከ ምሽቱ 3፡15 ድረስ በቦታው መቆየቱንም ዘገባው አስነብቧል።

የ42 ዓመቱ አውሮፕላን አብራሪ ካሜሩ ምርመራ ሲደረግለት የኮሮና ቫይረስ ይገኝበታል፡፡ በወቅቱም በቬትናም ውስጥ በቫይረሱ የተያዘ 91ኛው ግለሰብ ሆኖ ተመዘገበ፤ ወደ ሆቺሚንህ ሆስፒታል በመሄድም ክትትሉን ጀመረ፡፡ ወደ ሆስፒታል በገባ በቀናት ልዩነት ውስጥ ካሜሩን ወደ ጽኑ ህሙማን ክፍል እንዲገባ ተደረገ፡፡ እስከ ዛሬ ሰኔ 21/2012 ዓ.ም ባለው መረጃ ካሜሩን በቬትናም በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ወደ ጽኑ ህሙማን ክፍል የገባ የመጨረሻው ሰው ነው።

በጽኑ ህመም ላይ እያለ ስለ አውሮፕላን አብራሪው የሚወጡ መረጃዎች መልካም አልነበሩም። ወደ 95 ሚሊዮን ዜጎች ያሏት ቬትናም በመቶዎች የሚቆጠሩ የኮሮና ቫይረስ ታማሚዎች ቢገኙባትም አንድም ሰው በቫይረሱ አልሞተባትምና ምናልባትም በቫይረሱ የተነሳ የመጀመሪያውን ሞት ልታስመዘግብ ከቻለች በካሜሩን አማካኝነት እንደሚሆን ተሰግቶ ነበር፡፡

ቀናት ሳምንታትን እየተኩ፣ ሳምንታት ወራትን ደፍነው ከሁለት ወራት ከአንድ ሳምንት በላይ ተቆጠሩ፤ ካሜሩን ለ68 ቀናት በጽኑ ህሙማን ክፍል ቆዬ፡፡ በቬትናም ያሉ ሃኪሞችም የ91ኛውን የኮሮናቫይረስ ታካሚ ሕይወት የማትረፍ ጉዳይ አሳስቧቸዋልና ሁሌም በቪዲዮ ውይይት ይመክራሉ፡፡ የሃገሪቱ የጤና ሚኒስቴር ሰዎችም በተመሳሳይ ዋና አጀንዳቸው የስቴፈን ካሜሩን የነፍስ ውጪ ነፍስ ግቢ ሁኔታ ሆነ፡፡

ሃኪሞቹ በውይይታቸው በርካታ አከራካሪ ጉዳዮችን ቢያነሱም በአንድ ነገር ደግሞ መቶ በመቶ ይስማማሉ፤ ይህም ስቴፈን ካሜሩን በሕይወት የመትረፍ እድሉ 10 ከመቶ ብቻ ስለመሆኑ ነው። የስቴፈን ካሜሩን ጉዳይ የብዙዎች መነጋገሪያም ሆነ። የጤናው ሁኔታም ውስብስብ ሆነ። ሆስፒታል ከገባ በኋላ በቀናት ልዩነት ኩላሊቶቹ ሥራ አቆሙ፡፡ ሳንባውም ቢሆን ራሱን ችሎ አየር ማንሸራሸር ተስኖት እርዳታን ፈለገ፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የኩላሊት እጥበት እየተደረገለት፣ በአጋዥ መሳሪያ (ቬንትሌተር) እየተነፈሰ በሞትና በሕይወት መካከል ሆኖ 68 ቀናትን አሳለፈ፡፡

የካሜሩንን እስትንፋስ ለማስቀጠል ከህጻን እስከ 70 ዓመት ያሉ የእድሜ ባለጸጎች ትብብር አድርገውለታል፤ የቬትናም ዶክተሮችም እንቅልፍ አጥተው እየተረባረቡለት ነው፡፡ ታካሚው ከነበረው ክብደትም 20 ኪሎ ግራም ቀንሷል፡፡ በዚህ ጊዜ ሃኪሞች ተስፋ ወደ መቁረጥ ሄዱ፤ 91ኛው የኮሮና ቫይረስ ታካሚ የመጀመሪያዉ ሟች ሊሆን ከጫፍ ደርሷል፡፡

ካሜሩን ወደ ጽኑ ህሙማን ክፍል በገባ በ68ኛው ቀን ግን ድንገተኛ የሆነ ለውጥ ማሳየት ጀመረ፡፡ በሃኪሞቹ ፊትም የደስታ ጸዳል ፈነጠቀ፡፡ ልፋታቸው ፍሬ እንዳፈራ አሰቡ፡፡ ድንገተኛ ስብሰባም ተደረገና ስለ ውጤቱ ተነጋገሩ፡፡ የካሜሮን ሕይወት የመትረፏ ጉዳይ ከተስፋም በላይ እርግጥ ሆነ፤ አዎ! ለ68 ቀናት በሕይወትና በሞት መካከል የቆየው የ42 ዓመቱ አውሮፕላን አብራሪ ዳግም የመኖር ተስፋው እውን ሆነ። ከፈጣሪ በታች ምስጋና ሕይወታቸውን አስይዘው ሕይወታችንን ለሚታደጉልን ሀኪሞች ይሁንና ዳግም የመኖር ዕድል ያገኘው ስቴፈን ካሜሩን በቅርቡ ከቤተሰቦቹ ጋር መገናኘትን ያልማል፡፡

“በየትኛውም ዓለም ላይ ብሆን ኖሮ ሕወቴ ያልፍ ነበር” ሲልም ካሜሩን ለቬትናም ሀኪሞች ያለውን አክብሮት እየገለጸ ነው፡፡ “የቬትናም ሀኪሞች በህሊናየ ሳይሆን በእያንዳንዷ የደም ጠብታዬ የተዋሃዱ ናቸው” ሲልም አመስግኗቸዋል።

በኤልያስ ፈጠነ

Previous articleበአማራ ክልል ተጨማሪ አንድ ሰው የኮሮናቫይረስ ተገኘበት።
Next articleበኮሮናቫይረስ ምክንያት የሟቾች ቁጥር ከግማሽ ሚሊዮን አለፈ፡፡