
ባሕር ዳር: ጥር 11/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የጥምቀት በዓል በጎንደር ከተማ እየተከበረ ይገኛል። በዚህ በዓል ላይ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ እንደተናገሩት የጥምቀት በዓል ከሃይማኖታዊ ይዘቱ ባለፈ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያለው በዓል ነው፡፡
ርእሰ መሥተዳድሩ ቤተ ክርስቲያኗ አማኞቿን በበጎ ሥነ ምግባር ኮትኩታ በማሳደግ በሀገር ግንባታ፣ በኢኮኖሚው እና በቱሪዝም ልማት አካባቢው እንዲሻሻል በማድረግ ትልቅ አስተዋጽኦ ያደረገች መኾኗን ተናገረዋል፡፡
ጎንደር እና አካባቢው የኢንቨስትመንት ቦታ እንዲኾን በማድረግ ብሎም ማኅበረሰቡ ማኅበራዊ ሕይወቱን እንዲያጠናክር ጥምቀት ትልቅ አስተዋጽኦ እያደረገ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡
ጎንደር በልዩ ሁኔታ እያከበረች ያለውን የከተማዋን መገለጫ የኾነውን ጥምቀት ሥርዓቱን በጠበቀ መንገድ አክብሮ ለቀጣይ ትውልድ ማሳተላለፍ እንደሚገባም ገልጸዋል፡፡
ጥምቀት የሰላም በዓል በመኾኑ ሕግን ለማክበር እና ሰላምን ለመጠበቅ ቃል የሚገባበት እንደኾነም አስረድተዋል፡፡
“የጎንደር የመታደስ ጊዜ መጥቷል” ያሉት ርእሰ መሥተዳደር አረጋ ከበደ ጎንደር ቀደም ሲል ለመላው ሀገሪቱ ሥልጣኔ አብሪ ኮከብ እንደኾነች ሁሉ በዚህ ዘመንም ያጋጠማትን ጉስቁልና አራግፋ አሁን ውብ ኾና በመታደስ ላይ እንደምትገኝም አብራርተዋል፡፡
ጎንደር በለውጧ ለሌሎች አካባቢ ምሳሌ ልትኾን በጽናት መቆሟንም ተናግረዋል፡፡ ጎንደር የቀደመውን ችግር ማራገፍ ብቻ ሳይኾን እንደሌሎች የዓለም ከተሞች የሕዝቦቿን ዕድገት በሚመጥን መንገድ ራሷን አድሳ ለነዋሪዎቿ እና ለጎብኝዎቿ ምቹ ለማድረግ ርዕይ ሰንቃ በጽናት መቆሟን አስረድተዋል፡፡
የጎንደር ሕዝብ እና የጎንደር ወዳጅ የልማት አጋሮች ከተማዋን ለማልማት ቆርጠው ስለመነሳታቸውም ነው ያብራሩት፡፡
ጎንደር መንገዷ መድመቁን መሐሏ መፍካቱን ገልጸው አሁንም መስፋት እንደሚገባት አስረድተዋል፡፡ ለዚህም ጎንደርን ለማልማት ሁሉም እንዲረባረብ ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡
ዘጋቢ:- ምሥጋናው ብርሃኔ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
