
ባሕር ዳር: ጥር 11/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የጥምቀት በዓል በጎንደር በአፄ ፋሲለደስ ጥምቀተ ባህር እየተከበረ ነው። በበዓሉ ላይ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የውጭ ሀገር ዜጎች፣ የእምዕነቱ ተከታዮች ታድመዋል።
በበዓሉ የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ቻላቸው ዳኘው እንዳሉት የዘመናዊቷ ጎንደር ከተማ መሥራች አጼ ፋሲለደስ ያስገነቡት የመጠመቂያ ገንዳ የጎንደርን ጥምቀት ልዩ ያደርገዋል። ጎንደር የበርካታ ቅርሶች ባለቤት ስለመኾኗም ተናግረዋል።
ጥምቀት በጎንደር ሥርዓቱን በቃል ለመግለጽ በማይቻል ድምቀት የሚከበር በዓል ስለመኾኑም ጠቅሰዋል። ጥምቀት በጎንደር በርካታ ታሪካዊ ዳራዎች ያሉት፤ የበዓሉ አከባበርም የከተማዋን ታሪካዊነት የሚገልጽ እና የነዋሪዎቿን ወገን ወዳድነት ለእንግዶች የሚገልጥ ነው ብለዋል።
ጥምቀት የአብሮነት በዓል ነው ያሉት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ጥምቀትን ስናስብ መለያየትን በአንድነት፤ ጥልን በፍቅር፣ መፍረስን በመገንባት፣ ጨለማን በብርሃን፣ ድህነትን በብልጽግና ድል መንሳት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል። ሀገራችንን ወደከፍታ የሚያሻግራትን እምነት፣ ተስፋ እና ፍቅር ይዘን በዓሉን ማክበር አለብንም ብለዋል።
ጎንደር ከትላንት እስከ ዛሬ የኢትዮጵያ ሥልጣኔ፣ አንድነት እና ክብር ተምሳሌትነቷ በተግባር የተገለጠ ነው ሲሉም ተናግረዋል።
ከድህነት እና ኋላቀርነት የምንላቀቅበት፣ የሀገራችንን ብልጽግና ለማረጋገጥም በተሰለፍንበት ሁሉ የምንተጋበት ጊዜው አሁን በመኾኑ ያለልዩነት አብረን ቆመን በጋራ መሥራት አለብን ሲሉም ጥሪ አስተላልፈዋል።
የጥምቀት በዓል በዓለም የምንታወቅበት ታላቅ በዓል ነው፤ በዓሉን በአንድነት እናክብር ሲሉም መልእክት አስተላልፈዋል።
ዘጋቢ፦ አሚናዳብ አራጋው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
