
ባሕር ዳር፡ ጥር 10/2018ዓ.ም (አሚኮ) በባሕር ዳር ከተማ የጥምቀት ከተራ በዓል በልዩ ልዩ ሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓቶች እየተከበረ ነው። በበዓሉ ታላላቅ የሃይማኖት አባቶች፣ የከተማ አሥተዳደር መሪዎች እና የሃይማኖቱ ተከታዮች ታድመዋል።
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው በቦታው ተገኝተው መልዕክት አስተላልፈዋል። ጥምቀት ሃይማኖታዊ እና ባሕላዊ እሴቶች የሚገለጡበት መኾኑን ተናግረዋል። “ጥምቀት ኢትዮጵያን የማሳያ ሙዚየም ነው” ሲሉም ተደምጠዋል።
ጥምቀት የማኅበራዊ መስተጋብር መገለጫ ነው ያሉት ከንቲባው በዓሉ ኅብረ ብሔራዊ በዓልም መኾኑንም ገልጸዋል።
በአልባሳት አምረን የምንታይበትን በዓል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ለትውልድ ለማስተላለፍ የምታደርገውን ጥረትም አድንቀዋል።
ባሕር ዳር ከተማ በልዩ ልዩ ልማቶች እያማረች መኾኑንም ተናግረዋል። ከተማዋ የተለያዩ የቱሪዝም ኮንፈረሶችን የምታስተናግድ በመኾኗ ሰላሟን ልንጠብቅ ይገባል ነው ያሉት።
ጥርን በባሕር ዳር በደመቀ ሁኔታ እንዲከበር እያደረጉ ለሚገኙ የማኅበረሰብ ክፍሎች እና ለጸጥታ አካላትም ምሥጋና አቅርበዋል።
ባሕር ዳር ለሃይማኖታዊ በዓላትም ተመራጭ እንድትኾን ሀገረ ስብከቱ እየሠራ ያለውን ሥራ አድንቀው ከተማ አሥተዳደሩም ድጋፉን አጠናከሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።
ዘጋቢ፦ ደመወዝ የቆየ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
