የከተራ በዓል ሲከበር በመተሳሰብ እና በመረዳዳት ሊኾን ይገባል።

4
ገንዳ ውኃ፡ ጥር 10/2018ዓ.ም (አሚኮ) በምዕራብ ጎንደር ዞን የከተራ በዓል በድምቀት በገንዳ ውኃ ከተማ እየተከበረ ነው።
ከተራ ማለት ከተረ ወይም ከበበ ከሚለው የግዕዝ ግሥ የወጣ ሲኾን ፍችው ውኃ መከተር፣ መገደብ ማለት ነው ያሉት የምዕራብ ጎንደር ዞን ሀገረ ስብከት ትምህርት እና ሥልጠና ክፍል ኀላፊ መጋቢ ሃይማኖት ፍሬአሚን ጌቴ ናቸው።
የጥምቀት ዋዜማ ታቦተ ሕጉ ከቤተ መቅደስ ወጥቶ ውኃ ባለበት አካባቢ ስለሚያድር አማኙ ሕዝብ እየተሠበሠበ በወንዝ ዳር አካባቢ ድንኳን ይተክላል ብለዋል።
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዮሐንስን አስከትሎ ሊጠመቅ ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ የመሄዱ እና ለመጠመቅ ተራ ሲጠብቅ እዛው የማደሩ ምሳሌ እንደኾነ ገልጸዋል።
በእደ ዮሐንስ በፈለገ ዮርዳኖስ ለመጠመቅ ከማታው ጀምሮ መውረዱን እና ተሰልፎ ተራውን ሲጠብቅ ማደሩን ለማስታወስ እንደኾነ አንስተዋል።
የጥምቀት በዓል የምናከብረው ፍጥረታትን የፈጠረ አምላካችን ጌታችን እና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዮርዳኖስ ወንዝ ራሱን ዝቅ አድርጎ ከዮሐንስ ዘንድ የተጠመቀበት የትህትና መገለጫ ምክንያት በማድረግ እንደኾነ አብራርተዋል።
ኢየሱስ ክርስቶስ የተጠመቀው የሰውን ልጆች ሁሉ ከሀጢዓት ነፃ ለማውጣት እና ለሰው ልጆች ሁሉ አርዓያ ለመኾን ነው፤ ስለኾነም የጥምቀት በዓል ሲከበር በመተሳሰብ እና በአብሮነት ሊኾን ይገባል ብለዋል።
የበዓሉ ተሳታፊ ወጣት ገብሬ ባሕሩ እንደተናገረው የከተማው ወጣቶች ከትናንት ምሽት ጀምሮ የታቦታቱን መውረጃ መንገዶችን በማጽዳት እና ዛሬም ታቦታቱን በማጀብ ሸራ በማንጠፍ ሥራዎችን እየሠሩ እንደኾነ ጠቁሟል።
በማስተባበር ታቦተ ሕጉ በሰላም ወደ ባህረ ጥምቀቱ ማረፊያቸው እንዲገቡ የበኩላቸውን እንደሚወጡም ገልጸዋል።
ሌላኛው ተሳታፊ ወጣት እንዳለው ዘውዱ እንደሚለው በዚህ ዓመት እየተከበረ ያለው የከተራ በዓል ሃይማኖታዊ እና ባሕላዊ ትውፊቱን በጠበቀ መንገድ ከባለፈው ዓመት በተሻለ መንገድ እያከበሩ እንደኾነ ተናግሯል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous article‎ጥምቀት ምንድን ነው? ለምንስ በውኃ ኾነ?
Next article‘’ጥምቀት ኢትዮጵያን የማሳያ ሙዚየም ነው’’ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው