
ባሕር ዳር: ጥር 10/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የጥምቀት በዓል ከሃይማኖታዊ ክዋኔው በተጓዳኝ ባሕላዊ ክዋኔዎቹም ትኩረትን ይስባሉ።
ጥምቀት በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባሕል ድርጅት (ዩኔስኮ) የማይዳሰስ የዓለም ቅርስነት እንዲመዘገብ ካደረጉት ነገሮች መካከል ሃይማኖታዊ እና ባሕላዊ ክዋኔዎቹ እና እሴቶቹ ናቸው።
በጥምቀት በዓል ዋዜማ (በከተራ ሥርዓት) ታቦትን ከመንበሩ ወደ ጥምቀተ ባሕሩ መውሰድ እና ወደ መንበሩ የመመለስ ሥርዓት ታቦት እጀባ ይባላል።
ታቦትን አጅቦ መጓዝ ሃይማኖታዊ ትዕዛዝ መኾኑን ያብራሩልን መጋቢ ምሥጢር ስማቸው ንጋቱ ናቸው።
በየዓመቱ በሚከበረው የጥምቀት በዓል ታቦታት ከመንበራቸው ወጥተው ወደ ከተራው ቦታ ሄደው የሚያድሩት የክርስቶስን ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ መጓዝ ለመዘከር መኾኑን ገልጸዋል።
ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ዮርዳኖስ ወርዶ እንደተጠመቀ ሁሉ ዛሬም ወጣቶች፣ ጎልማሶች እና ሽማግሌዎች ታቦታትን ይዘው በኾታና በእልልታ አጅበው ያደርሳሉ ብለዋል።
በመጽሐፈ እያሱ ምዕራፍ 3፥3 ላይ እንደተጻፈው የእግዚአብሔርን የቃል ኪዳኑን ታቦት ሌዋውያን ካህናት ተሸክመው ስታዩ ከየሠፈራችሁ እየወጣችሁ ተከተሉት፤ አጅቡት፤ እንደሚል ጠቅሰዋል።
በዚህም መሠረት ታቦት በሕዝበ እስራኤል እልል እየተባለ ታጅቦ ይንቀሳቀስ እንደነበርም ተናግረዋል።
በመኾኑም ታቦታት ለጥምቀት ወደ ከተራው ሲሄዱ እና ሲመለሱ ነገሥታት ሁሉ ከሕዝቡ ጋር ኾነው በእልልታ እንደሚያጅቡ ነው የገለጹት።
የታቦት እጀባውም ሥርዓት አለው ያሉት መጋቢ ምሥጢር ስማቸው ሕዝቡ ወደ ታቦቱ እንዳይጠጋ እያሱ ማስጠንቀቁንም አንስተዋል።
ሴቶች፦
በኾት ያግባህ በኾት፤
ያገራችን ታቦት፤ እያሉ
ወንዶች ደግሞ በኾታ፣ በፈረስ ግልቢያ፣ ባለመሣሪያዎች በሠልፍ ሥርዓት በማጀብ እንደሚያከብሩት ነው የጠቀሱት።
‘ለጥምቀት ያልኾነ ቀሚስ ይበጣጠስ’ የሚባልለት በጥምቀት በዓል ሴቶች የተለየ የአለባበስ ሥርዓት አላቸው። የክት ልብስ ለብሰው እና ተውበው የሚወጡበት ቀን ነው።
ታላላቅ አባቶች እና ዲያቆናት ጥላ ይዘው ከታቦቱ ፊት ለፊት በመሄድ በማዕጠንት ያጥናሉ። ቀጥሎም ለታቦቱ ጥላ ይዘው የሚያነግሡ እና የሚያከብሩ ይከተላሉ። በርቀት መዘምራን ካህናት፣ ቀጥሎም ሕዝቡ ዙሪያውን ከብቦ እየተከተለ በፈረሰኞች እየተከበከበ ይጓዛል።
ባለመሣሪያዎች ደግሞ መሣሪያቸውን ወላውለው፣ የክት ለብሰው እና አጊጠው፣ ዝናራቸውን ታጥቀው ከታቦቱ ራቅ ብለው እየመሩ አጅበው ይጓዛሉ።
ሕዝቡ በዜማዎች ፈጣሪውን እያመሰገነ፣ የማኅበረ ቅዱሳን ዘማርያን እየዘመሩ፣ በገና እየደረደሩ እና እንቢልታ እየተነፋ ለታቦቱ ክብር የደመቀ እጀባ ይደረጋል።
ይህ መነሻው ሃይማኖታዊ የኾነ ባሕላዊ የአከባበር ሥርዓት ከሌሎች ሀገራት በዓል የተለየ በመኾኑ ነው በዩኔስኮ የተመዘገበው ያሉት መጋቢ ምሥጢር ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ከእጀባው ጋር የሚቀላቀሉ የንግድ ሥራ እና ሌሎች ሃይማኖታዊ ያልኾኑ ድርጊቶች ሊስተካከሉ እንደሚገባ አሳስበዋል።
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በባሕር ዳር ሀገረ ስብከት የጽዋ ማኅበራት ኅብረት ሕዝብ ግንኙነት ኀላፊ ወጣት ዘላለም አክሊሉ ወጣቶች በጥምቀት በዓል እጀባ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳላቸው ገልጿል።
ወጣቶች በዓለማዊም ኾነ በመንፈሳዊ አገልግሎት ለበዓሉ ድምቀት ከልቡ ይሠራል። ከዋዜማው ጀምሮ መንገዶችን በማጽዳት እና በማደላደል፣ አባቶች የሚያዝዙትን በመሥራት፣ ሰላም በማስከበር፣ በመንፈሳዊ ዜማ እና ሽብሻቦም በዓሉን ያደምቃሉ ነው ያለው።
የተለያዩ የወጣቶች አደረጃጀቶች በመናበብ በዓሉ ሰላማዊ እና ትውፊቱን የጠበቀ እንዲኾን ለማድረግም እንሠራለን ያለው ወጣት ዘላለም አንዳንድ መጤ ልማዶችን እና ከቀናነት በሚመነጭ የሚታዩ ስህተቶችን ለማስተካከል እየሠራን ነው ብሏል።
ዘጋቢ፦ ዋሴ ባየ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
