
ባሕር ዳር፡ ሰኔ 21/2012 ዓ.ም (አብመድ) በአማራ ክልል ባለፉት 24 ሰዓታት ለ 451 ናሙናዎች የላቦራቶሪ ምርመራ ተደርጎ አንድ ግለሰብ የኮሮናቫይረስ ተገኝቶበታል።
ቫይረሱ የተገኘበት የ23 ዓመት ወጣት ነው። ይህም በደቡብ ወሎ ዞን ወረኢሉ መናኸሪያ ውስጥ በተደረገ ድንገተኛ የናሙና ምርመራ የተገኘ መሆኑን የክልሉ ጤና ቢሮ አስታውቋል።
በአማራ ክልል ባለፉት 24 ሰዓታት ያገገመ፣ በቫይረሱ ምክንያት ሕይወቱን ያጣም ሆነ ወደ ጽኑ ሕሙማን ክፍል የገባ አለመኖሩን ቢሮው አስታውቋል። ቫይረሱ ተገኝቶባቸው በለይቶ የህክምና መስጫ ማዕከላት ውስጥ የሚገኙት ሁሉም ሰዎች በመልካም ጤንነት እንደሚገኙም ጤና ቢሮው አስታውቋል።
በክልሉ እስከ ዛሬ ሰኔ 21/2012 ዓ.ም ድረስ ለ14 ሺህ 406 ሰዎች የናሙና ምርመራ ተደርጓል፤ በ308 ሰዎች ላይ ቫይረሱ መገኘቱም ተረጋግጧል። 99 ሰዎች ከበሽታው አገግመዋል፣ ሁለት ሰዎች ደግሞ በቫይረሱ ምክንያት ሕይወታቸውን አጥተዋል።
በብልሽት ምክንያት ሥራ አቁሞ የነበረው የጎንደር ናሙና መመርመሪያ ማሽን ሥራ መጀመሩን እና በ24 ሰዓታቱ ውጤት ማሳወቁን ቢሮው አስታውቋል።
በደጀኔ በቀለ