
ባሕር ዳር: ጥር 10/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የአደረጃጀት ዘርፍ ባለፉት ስድስት ወራት የተከናወኑ ተግባራትን ገምግሟል።
በመድረኩ ከዞኖች፣ ከከተማ አሥተዳደሮች እና ወረዳዎች የመጡ የአደረጃጀት ዘርፍ መሪዎች ተሳትፈዋል።
በልጽግና ፓርቲ የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የአደረጃጀት ዘርፍ ኀላፊ ፍስሐ ደሳለኝ “ለጠንካራ ፓርቲ ጠንካራ አደረጃጀት ያስፈልጋል” ብለዋል። ባለፉት ስድስት ወራት ጠንካራ አባላት፣ መሪዎች እና ተቋም ለመገንባት የሚያስችል እቅድ ተዘጋጅቶ ወደ ተግባር መገባቱን አንስተዋል።
አደረጃጀቶችን በማጠናከር የታቀዱትን እቅዶች በውጤታማነት ለመፈጸም ርብርብ መደረጉንም አንስተዋል። በዚህም ውጤት ማስመዝገብ ተችሏል ነው ያሉት። በልማት እና በመልካም አሥተዳደር ተግባራት በየደረጃው ያሉ መሪዎች እና አባላት ግንባር ቀደም ተሳታፊ እንዲኾኑ ለማድረግ ጥረት መደረጉንም ገልጸዋል።
ለመሪዎች እና ለአባላት በርካታ ሥልጠናዎች መሰጠቱንም ጠቁመዋል። በመሪዎች ምደባ እና ስምሪት ላይም ሰፊ ሥራዎች ተሠርተዋል ብለዋል። በተልዕኮ ላይ ግልጽነትን በመፍጠር እና ስምሪት በመስጠት ኀላፊነታቸውን ባልተወጡ መሪዎች ላይ እርምጃ በመውሰድ የማጥራት ተግባር እንደተከናወነም ገልጸዋል።
የደቡብ ወሎ ዞን ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የአደረጃጀት ዘርፍ ኀላፊ ሀና አለባቸው በዞኑ ያሉት አደረጃጀቶች በተሟላ አሠራር እንዲገቡ መደረጉን ተናግረዋል። አባላትም ግንባር ቀደም በመኾን የመንግሥት ሥራዎችን እንዲያከናወኑ ለማድረግ የተጠናከረ ክትትል እና ድጋፍ መደረጉን አንስተዋል።
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የአደረጃጀት ዘርፍ ኀላፊ ጌታቸው ግዛቸው መድረኩ ያለፉትን ወራት አፈጻጸም በመገምገም ለቀጣይ አፈጻጸም ግብዓት የተወሰደበት ነው ብለዋል።
አደረጃጀቶችን በማጠናከር በመልካም አሥተዳደር እና በልማት እንቅስቃሴዎች ግንባር ቀደም ተሳታፊ እንዲኾኑ የማድረግ ሥራም ተከናውኗል ነው ያሉት።
ዘጋቢ:- አሰፋ ልጥገበው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
