
ባሕር ዳር: ጥር 10/2018 ዓ.ም (አሚኮ) እያንዳንዱ ሰው ስለ ጥምቀት በዓል ቢጠየቅ የኾነ ትዝታ ይኖረዋል። ለዛሬ ግን ሁለት የዕድሜ ባለጸጋዎችን የትናንት ትዝታቸውን ከዛሬው ሁነት ጋር በንጽጽር እንዲህ አጫወቱን።
እማሆይ የሺወርቅ አስረስ ይባላሉ፤ የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪ ናቸው። የጥምቀት በዓልን ነፍስ ካወቁበት ጊዜ ጀምሮ ለ85 ዓመታት ገደማ እያከበሩ እንደሚገኙ የትናንት ዘመናቸውን የኋሊት አስታወሱን።
በቆየው ዘመን አዲስ ዓመት ሲብት የጥምቀት በዓልን ለማክበር ዝግጅት ይጀምሩ እንደነበር እማሆይ የሺወርቅ አጫውተውናል። ጥምቀትን ተውበው እና ደምቀው ለማክበር አንዳንድ ነገሮችን ማሟላት የግድ ነው ባይ ናቸው።
በቆሎ ታጭዶ ሲከመር ወዳድቆ የሚቀር በቆሎ በመሰብሰብ፣ ከአውድማ እህል በመውሰድ፣ ቅቤ እና ዕንቁላል በመሸጥ የሚቋጥሩትን ገንዘብ በማጠራቀም ማለፊያ የተዥጎረጎረ መቀነት ያሠሩበታል፤ ቀሚሳቸውን ያስጠልፉበታል፤ ነጠላ ያስቋጩበታል።
ጸጉራችን ለጥምቀት ጋሜ እና ሳዱሌ ተላጭተን በአደስ ቅቤ እናረሰርሰው ነበር ያሉት እማሆይ የሺወርቅ ለእጃቸው አምባር እና ድኮት ለእግራቸው አልቦ እና ስንድድ፣ ለአንገታቸው መስቀል፣ ድሪ እና እርባን ማዘጋጀት የጥምቀት ሰሞን ተግባራችን ነበር በማለት ትናንትን አጫወቱን።
እኔ “ጥልፍ ቀሚስ ስለሌለኝ የእናቴን ለብሼ ያከበርኩበትን ጊዜ አልረሳውም” ነው ያሉት እማሆይ የሺወርቅ። ትርፍ ልብስ እና የመዋቢያ ቁሳቁስ ያለው ለሌለው ማዋስ የተለመደ ነበር ብለዋል።
የአንድ መንደር ልጆች እንሶስላ በጋራ በተዋጣ ገንዘብ ገዝተን በጋራ ሰብሰብ ብለን እንሞቅ ነበር ያሉት እማሆይ የሺወርቅ ጥምቀትን ዛሬ ድረስ ንጹሕ ለብሶ እና አጊጦ ማክበሩ ያስቀናኛል ሲሉ ትውስታቸውን ነገሩን።
በከተራ በዓል ደግሞ፦
“በወት ግባ በወት፣
ያገራችን ታቦት።
“አሰይ ስለቴ ሰመረ፣ ለመድኃኔዓለም ነግሬው ነበረ”። እያሉ ሲያዜሙ የማያጨበጭብ እጁ የሚቆረጥ፣ እልል የማትል ምላስ የምትታጠፍ እና አንደበቷ የሚቆለፍ ይመስል እንደነበር ድምቀቱን አነጻጽረው አስታውሰዋል።
ጎበዛዝቱ ልጃ ገረዶችን፤ ልጃገረዶች ጎበዛዝቱን በፍቅር መፈላለጉስ? አልናቸው።
በጥምቀት በዓል ልጃገረዶች ሰብሰብ ብለን ወዲያ ማዶ የሚወርፉንን ወንዶች፦
“ጸጉርህም ሸበተ አለ ገባ ገባ፣
እንደ አያቴ ጎበጥህ ሳታጭ ሳታገባ” እያሉ በውብ ቅላጼ ፍቅራቸውን በሰላም ይገልጹ እንደነበር ነግረውናል።
“ዛሬስ?” አልናቸው። “ዛሬማ! ሰው ነጭ በነጭ መልበስ ትቶ የተዥጎረጎረ ነው። ዘፈኑ ሁላ ፈረንጅኛ እየኾነ ማስተዋላቸውን ጠቆሙልን። ብዙም እንደማይገባቸውም ገለጹልን።
ሌላው የእድሜ ባለጸጋ አባ ታምራት ደስታ ይባላሉ፤ እርሳቸው በርካታ የበዓል ትዝታ እንዳላቸው ነግረውናል። ጥምቀትን ሲያስቡ መቼ የከብት ጥበቃ ተራ እንደሚደርሳቸው ያስቡና ተራቸው በጥምቀት ከኾነ ተራ ለመቀየር የማይፈነቅሉት ድንጋይ እንዳልነበር አይረሳቸውም።
“አዲስ በሳሪያን ቅድ የተሰፋ ኮት፣ እጀ ጠባብ እና ሱሪ እለብስና ነጭ ጋቢ እደርብበታለሁ። ጸጉሬን በፎጣ በመጠምጠም ቀጭን ዘንግ በመያዝ ወደ ጥምቀት እወርዳለሁ” ነው ያሉት።
በጥምቀት የውቧን ኮረዳ ቀልብ ለመግዛት ያደርጉት የነበረውን መሽቀርቀር ዛሬ ላይ ሲያስቡት ግርም እንደሚላቸው ነው ያጫወቱን።
“ፈልጌያለሁ ቆንጆ፣ ፈልጌያለሁ ቆንጆ፣
ውኃ ምታጣጣ የምትወጣ ጎጆ” እንል ነበር ሲሉም ትናንትን ዛሬ ላይ ነገሩን። ፍቅርን በዘፈን ይገልጻሉ እንጅ በቡድን የሚደረግ ጸብ አልነበረም ባይ ናቸው።
በቡድን መጨፈሩ፣ በየመንደሩ እየተዘዋወሩ መዝፈኑ፣ በቡድን ዘፍነው የሚያገኙትን ገንዘብ በቡድን እንደሚደሰቱበት አባ ታምራት ተናግረዋል።
በጥምቀት በዓል ትንሽ ትልቁን፤ ወንዱ ሴቷን፤ አዋቂው ሕጻኑን ሰው ለሰው ይንከባከብ ነበር ብለዋል። የሚጠፋፋ ሰው አልነበረም። ተንኮል፣ ምቀኛ እና ሸረኛ አልነበረም አልነበረም።
የአሁኑ ትውልድ የቆየውን ባሕል እና ወግ የሚያስቀጥል እንዲኾንም ተመኝተዋል።
በሙሉጌታ ሙጨ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
