
ባሕር ዳር: ጥር 10/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የጥምቀት በዓል ኢየሱስ ክርስቶስ በፍጹም ትሕትና ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ ተጉዞ በአገልጋዩ በቅዱስ ዮሐንስ እጅ የተጠመቀበትን ዕለት የሚከበርበት በዓል ነው፡፡
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በድምቀት ከሚከበሩት የዓደባባይ በዓላትም አንዱ ነው። በተለየ ሁኔታ ከሚከበርባቸው አካባቢዎች ውስጥ ደግሞ ላሊበላ ይገኝበታል።
ቅዱስ ላሊበላ በኢየሩሳሌም የ13 ዓመታት ቆይታው የክርስቶስን ከጽንሰቱ እስከ እርገቱ ያለውን በማየት እና ብሉይ እና ሐዲስን በማንበብ ትርጉማቸውን በዳግማዊት እየሩሳሌም ደብረ ሮሐ በውቅር አብያተ ክርስቲያናቱን ያስቀመጠ ቅዱስም ንጉስም እንደኾነ ይነገራል።
ትርጉማቸውን ከማስቀመጥ ባለፈ የኢየሱስ ክርስቶስን የልደት እና የጥምቀት በዓላት በድምቀት እንዲከበሩ ተደርጓል።
የላሊበላ ከተማ አሥተዳደር ባሕል ቱሪዝም እና ስፖርት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ዲያቆን አዲሴ ደምሴ በላሊበላ ታቦታቱ ወጥተው ማደር የጀመሩት በቅዱስ ላሊበላ ዘመን መኾኑን ገልጸዋል። በዘመኑ አብያተ ከርስቲያናት በተናጠል ይፈጽሙት የነበረውን ክብረ በዓል በማስቀረት ተሰባስበው በአንድ ጥምቀተ ባሕር እንዲያከብሩ ስለመደረጉም አስረድተዋል።
አሁን ላይም ከ11ዱ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት የሚገኙ ታቦታት በካሕናት፣ በዲያቆናት፣ በሰንበት ትምህርት ቤት ተማሪዎች እና በምዕመናን ታጅበው ወደ አምሳለ ዮርዳኖስ ባሕረ ጥምቀቱ ከደረሱ በኋላ ሥርዓተ ማሕሌት እና ሥርዓተ ቅዳሴ ሃይማኖታዊ ክዋኔዎች ይከናወናሉ ብለዋል።
ታቦታት ከጥምቀተ ባሕር ተነስተው ወደ መንበራቸው እስኪገቡ ድረስ ባሉት ቦታዎች በልዩ ዝማሬ፣ ሽብሸባ፣ እንደሚከወንም ገልጸዋል። በርከት ያሉ ካሕናት በያሬዳዊ ዝማሬ የሚያከብሩት ልዩ በዓል ነው። በተለይም ደግሞ ካሕናቱ የሚያቀርቡት ወረብ እና ዝማሬ በዓሉን ይበልጥ ያደምቀዋል ነው ያሉት።
በዓሉን ለማክበር ከቤተክርስቲያኗ እና ከማኅበረሰቡ ጋር በመቀናጀት ታቦታቱ የሚያድሩበትን ቦታ የማጽዳት፣ የማዘጋጀት እና አስፈላጊ ግብዓቶችን የማሟላት ሥራ መሠራቱንም ገልጸዋል።
ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
