እንግዲህማ ጥምቀት መጣ።

4
ባሕር ዳር: ጥር 10/2018 ዓ.ም (አሚኮ) እንግዲህማ ጥምቀት መጣለት፤ ጡሩምባ ቀን ወጣለት፤ ተንጠልጥሎ ጭስ መጠጣት አበቃለት። ተሰቅሎ ከከረመበት ወረደ። በጨርቅ ተወልውሎ፣ እስትንፋስን ስቦ ታቦታቱን ማድመቅ ጀመረ።
ጡሩምባ በአፈጣጠሩ የእርሱ የኾነ እስትንፋስ የለውም፤ ትንፋሽ ከሰው ተብድሮ ከሰው በላይ እልል ብሎ ታቦታትን የሚያከብርበት መንገድ ይገርማል።
ግን እርሱ ምን ቸገረው! ቁና ቁና ትንፋሽ የሚሰጠው ሞልታል። ወጣቶች እና ጎልማሶች ልክ እንደጨቅላ ልጅ ይቀባበሉታል። ሳምባቸው እስኪወጠር ድረስ እስትንፋሳቸውን እያማጉ ያጫውቱታል።
የሚያወጣው ድምፅ በጭፈራው መሃል የወጣቶችን መጋፋት እና መላፋት ያሞቀዋል። የታቦታቱን ንግሥ የበለጠ ያደምቀዋል።
ይህ የትንፋሽ መሳሪያ የታቦታት ንግሥ ላይ መገኘት ዛሬ የጀመረው ተግባር አይደለም። ከጥንትም ከኦሪት ዘመን ጀምሮ የታቦታት ማጀቢያ በመኾን መንፈሣዊ ልሳንነቱን ያስመሰከረ ነው ይላል በፎክሚዲያ ዙሪያ ጥናቱን ያደረገው ጋዜጠኛ ታደሠ ፀጋ።
ጡሩምባ ከመንፈሳዊነቱ ባሻገር የኢትዮጵያውያን ቁሳዊ እሴት ነው። ጡሩምባ ከብረት እና ከነሐስ ከመሠራቱ በፊትም ኢትጵያውያን ከሸንበቆ፣ ከቀርቅሃ እና ከቅል በተለያየ ቅርፅ በመሥራት ይጠቀሙበት እንደነበር ጋዜጠኛ ታደሠ ያወሳል። ጡሩምባ ሥነ ተግባቦትም ነው ይላል ጋዜጠኛ ታደሠ።
ለሀዘን መርዶ የምንጠቀመው የጡሩምባ ድምፅ ለደስታ ለሠርግ ከምንጠቀመው ይለያል፤ ለሠርግ የምንጠቀመውንም የጡሩምባ ድምፅ ለታቦታት ንግሥ አንጠቀመውም፤ ለንግሥ የምንጠቀመው የጡሩምባ ድምፅ እንዲሁ ለአደጋ ጊዜ ጥሪ ከምንጠቀመው እንደሚለው ተናግሯል።
ይህንን ማኅበረሰባችን ጠንቅቆ ያውቃል፣ ለደስታ ነው ለሀዘን፣ ለንግሥ ነው ለትብብር የሚለውን የጡሩምባ ድምፅ ሰምቶ መልዕክቱን ይረዳል።
ታዲያ የጥምቀት እለት የጡሩምባው ድምፅ ከሁሉም ይለያል። ኑ ታቦታቱን አጅቡ ብሎ ይጣራል፤ በጭፈራው መሀል ገብቶ አቧራው ጨሰ ያስብላል። ወጣቶችን ላባቸው ጠብ እስኪል ጮቤ ያስረግጣል።
እግረ መንገዱን ግን ጡሩምባ መንፋት ቀላል አይደለም።
“የጡሩምባ ዚመት፤
የጡሩምባ ድምፀት፤
ላድማጩ ነው እንጂ፤
ለነፊው ሲቃ ነው…” እንዳለው ገጣሚው ለጥሩምባ ነፊው አስቸጋሪ ነው። ያም ኾኖ ለታቦታቱ ንግሥ ዋና ተዋናይ ነው፤ ለታቦት አክባሪ መግነጢሳዊ ነው፤ ለጥምቀት ትዝታም ጉልህ ማኅተም ነው፤ የዓመት ሰው ይበለን።
በደመወዝ የቆዬ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous article“የእንሶስላችን ትዝታ”
Next articleየተወዳጁ አርቲስት ነፃነት ወርቅነህ ሥርዓተ ቀብር ተፈፀመ።