“የእንሶስላችን ትዝታ”

4
ባሕር ዳር: ጥር 10/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ በድምቀት ከሚከበሩ ሃይማኖታዊ በዓላት መካከል የጥምቀት በዓል አንዱ ነው።
ይህ በዓል በሃይማኖታዊ ሥርዓቱ እና በባህላዊ ትውፊቱ ሚሊዮኖችን የሚያሰባስብ በመሆኑ በናፍቆት ይጠበቃል። ሁሉም በየ እድሜ ደረጃው አጊጦ እና ተውቦም በበዓሉ ይሳተፋል።
ሴቶች በጥምቀት በዓል አምረውና ደምቀው ለመዋል ከሚጠቀሙባቸው ማጌጫዎች መካከል እንሶስላ አንዱ ነው። እረ እንዴውም እንሶስላ የቁንጅና መገለጫም ነው። ለዚህም ማሳያው እንሶስላ መስለሻል የሚለው አገላለጽ ነው። እጅን እና እግርን ለማስዋብ የሚያገለግለው ባሕላዊ ማጌጫ እንሶስላ በቡድን የመሞቅ ሂደቱ ለሴቶች ልዩ ስሜትን የሚሰጥ እና የማይረሳ ትዝታን የሚያጎናጽፍ ክንውን ነው፡፡
እኔም የቅርብ ጊዜውን የእንሶስላ መሞቅ ትዝታ ተጋሪ ነኝ። አስታውሳለሁ ከበዓሉ ቀደም ባለ ጊዜ በሳንቲሞች ቢበዛ በአንድ ብር የተገዛን እንሶስላ ከተከመረ አመድ ወይም የከብቶች ተረፈ ምርት ሲደበቅ። ይህ የሚኾነው እንሶስላው እንዲይዝ ተብሎ ነው። በጥምቀት ዋዜማ የከተራ ቀን ረፋድ ላይ የተደበቀውን እንሶስላ በማውጣት ታዳጊ የሠፈር ልጆች ሰብሰብ ብለን በአነስተኛ መያዣ ይዘን በምንኖርበት ከተማ ጠርዝ ወደ ሚገኝ ወራጅ ወንዝ ለማጠብ እናመራ ነበር። አለት ላይ እየፈተግን በአመድ እና በጭድ በደንብ አጥበን በአለሎ ድንጋይ ጨቅጭቀን በእቃ አድርገን ይዘን ወደ ቤት እንመለሳለን።
የመሞቂያ ሰዓቱ እስከሚደርስ ፀሐይ ላይ አስጥተን ከቆየን በኋላ መሸት ሲል የሰፈር ልጆች እራታችን በልተን ሰፊ እና ለጨዋታ አመቺ ቤት ላይ ሰበሰብ ብለን ተገናኝተን በድስት እሳት ላይ ጥደን ሞቅ እያደረግን እንሶስላችን እንሞቅ ነበር። በምሽት እንሶስላ የመሞቁ ምስጢር ሲሞቅ ምች ያስመታል ስለምንባል ነበር። ጨረቃ እንዳታይብንም የማናደርገው ጥረት አልነበረም። ታዲያ በመሞቅ ሂደቱ ጠቆር ያለ ጓደኛ ከሌለን ለቀይ ሰው አናሳይም ነበር ሃ፣ሃ፣….ወደ ታች ደብቀን ነበር የምንሞቀው። ይህ እንግዲህ ቀይ ሰው ካየው እንሶስላው አይዝም፤ አይጠቁርም እየተባለ በትውፊት ስለሰማን ነው። አይ ልጅነት…
ከእንሶስላ መሞቁ ጎን ለጎን እንሶስላየ አበባየ እያልን በቡድን ዜማ እያዜምን፤ ገፋሽኝ! ገፋሽኝ! እየተባባልን እንሶስላ ስንሞቅ፣ ስንጫወት ከቆየን በኋላ ግማሹ በሞቀው በቃኝ ይላል። ግማሹ ደግም የበለጠ እንዲይዝ መዳፍ እና ጥፍር ላይ እንሶስላው አርፎ እጅ ተጠቅልሎና ታስሮ ያድራል። ድንገት የሚያሳክክ ነገር ከተፈጠረ ጉድ ፈላ ሃ፣ሃ፣… አጌጡ ሲሉ ተመለጡ የሚለው አባባል የሚሠራው እዚህ ላይ ነው ። በሁኔታው እየተሳሳቅን ብዙ ሳንተኛ ነበር ሌሊቱ የሚነጋው።
ጮራ ሳትወጣ የሞቅነውን እንሶስላ እጃችን ለብ ባለ ውኃ ታጥበን በዋዜማ ፈልገን ባዘጋጀነው ኩሸሽሌ በተባለ ተክል ደረቅ ቅጠል ወይም በደረቀ የአህያ ተረፈምርት እጃችን ይታጠናል፤ ከዛ ቅባት ይቀባል። እንዳይለቅ ማጠንከሪያ መኾኑ ነው።
በደንብ ያልያዘለት የቡድን አባል ካለ የወንድ እጅ፣ ሥራ የማይሠራ እየተባለ ይተረባል። እኔ የዚች ተረባ ገፈት ቀማሽ ነበርኩ። አስታውሳለሁ ይሄንን በመፍራት አንዳንዶች ከጥምቀት በዓል ቀደም ብለው ሠርተው የማያውቁትን ከባድ ሥራ ሁሉ እጃቸው እንዲሻክር ይሠሩ እንደነበር። በመጨረሻም ለጥምቀት የተገዛልን አዲስ ልብስ ለብሰን የተዋበው እጃችን ላይ ዓይናችን ሰረቅ እያደረግን እያየን አንዳንዴም ለሌሎች ለማሳየት የመፈለግ አይነት ስሜት እያሳየን ተውበን የጥምቀት በዓልን እናከብር ነበር።
ጊዜ ጊዜን እየወለደ ዘመናት ሲቀየሩ ግን ነባሩ ባሕል እየተለወጠ እና እየቀረ መጣ። በአጭር ጊዜ ከእንሶስላ ይልቅ ሂና የተባለ መዋቢያ ገነነ። እርሱም አልዘለቀም። እንሶስላም ኾነ ሂና የመሞቅ ፍላጎት ቀነሰ። የሚሞቅም እንደ ኋላቀር ተቆጠረ። ከራስ ይልቅ በሰው መድመቅን ምርጫችን አድርገን፤ አንድነትን፣ መዋደድን፣ መተሳሰብን የሚፈጥረው የእንሶስላ መሞቅ ባሕላችን በጥፍር ቀለም ቀየርን። እኔም የዚህ ሁሉ ሂደት ተካፋይ ኾንኩ።
የ76 ዓመት አረጋዊዋ ወይዘሮ የሕዝብ ጥላ ግን እድሜ ሳይገታቸው እና ባህላቸውን ሳይዘነጉ የጥምቀት በዓልን በሁሉም ዓመቶች ሳያሳልሱ እንሶስላ ሲሞቁ ነበር ። እንሶስላ መሞቅ ብቻ ሳይኾን የእንሶስላ አዘገጃጀት እና አሟሟቅ በነበረው ትውፊት አስቀጥለዋል። ዘንድሮም እርጅና እጅ ሳያሰጣቸው እንደ ልጅነታቸው ጊዜ ከጎረቤታቸው እና ወዳጃቸው ጋር በጨዋታ በታጀበው ህብረት እንሶስላ የመሞቅ ባህላቸውን አስቀጥለዋል።
ወይዘሮ የሕዝብ ከአሚኮ ጋር በነበራቸው ቃለመጠይቅ በልጅነት ጊዜያቸው እንሶስላን ከቤተሰብ አልፎ ጎረቤት ሰብሰብ ብሎ በጋራ የሚሞቅበት ሁኔታ እንደነበር ጠቆም አደረጉልን። ሳቁ፣ ጨዋታው፣ ትረባው ለጉድ ነበር ሲሉም በትዝታ ነጎዱ። እንሶስላ ሲሞቅ እናቶች ለብቻ ልጆች ለብቻ ኹኘው ነበር የሚሞቁት አሉን። ምክንያቱም በእሳት የተጣደውን እንሶስላ ሙቀት መቋቋም ግምት ውስጥ ይገባል። ምክንያቱም የልጆች እና የእናቶች ጨዋታም ይለያል።
በእንሶስላ መሞቅ ሂደት ውስጥ መዋብ፣ ጨዋታ እና ሕብረት ብቻ ሳይኾን መተሳሰብም አለ። የስጋ ዝምድና ባይኖርም ሁሉም ዘመድ ነው፤ ፍቅር እንጅ ጥላቻ ቦታ አልነበረውም። ወይዘሮ የሕዝብ የቀደመውን ባሕላዊ የውበት መጠበቂያ ባሕል ከአሁኑ ጋር እያነጻጸሩ ልዩነቱን ሲገልጹም አሁን ላይ ባሕሉ እየተቀረ እና እየቀረ መምጣቱን ጠቅሰዋል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እንሶስላውም እንደተጠቃሚው ጠፍቷል አሉን። በቀደመው ጊዜ በገጠር በአንዳንድ አካባቢዎች በየ ማሳው ይገኝ እንደነበር፤ ማግኘት ያልቻለ በአይተሽ ገብያ ገዝቶ ይሞቅ እንደነበር ነገሩን። ዛሬ ደግሞ ከተሜነት አይሎ እንሶስላ በኪሎ መሸጥ ጀምሯል። ዋጋው ከፍ ብሏል፤ በሳንቲም ቀርቶ በብዙ ብሮች ይሸጣል። እርሱም በጥቂት ቦታዎች ሲገኝ ነው።
ወይዘሮ የሕዝብ ግን እንኳን እንሶስላ ስጋም በአይተሽ ነበር የምንገዛው ብለው ያን ደግ ጊዜ አስናፈቁኝ። በዘመኑ በ25 እና በ50 ሳንቲም በስጋ የተሠራ ምግብ ሲበላ እንደነበር ነገሩኝ።
የኢትዮጵያውያን ባሕላዊ ማጌጫ እንሶስላ ባሕሉ እንዳይረሳ ሁሉም በየአካባቢው ባሕሉን ይዞ መቀጠል የአሁኑ ትውልድ አደራ ነው!
መልካም የከተራ በዓል!
ዘጋቢ፦ ሮዛ የሻነህ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous article“ኢትዮጵያ የምታስደንቅ ሀገር ናት” ከጣሊያን የመጡ ጎብኝዎች
Next articleእንግዲህማ ጥምቀት መጣ።