“ኢትዮጵያ የምታስደንቅ ሀገር ናት” ከጣሊያን የመጡ ጎብኝዎች

2
ባሕር ዳር: ጥር 10/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያ ዓለም ሊያያቸው ከሚጓጓላቸው ጥንታዊ እና ታሪካዊ ሀገራት መከካል ቀዳሚዋ ናት። የታሪካዊ፣ የመንፈሳዊ፣ የባሕልዊ እና ተፈጥሯዊ የመስህብ ሃብቶች ባለቤት የኾነችው ኢትዮጵያ የጎብኝዎችን ቀልብ ትስባለች።
ኢትዮጵያ የጎብኝዎችን ቀልብ ከምትስብባቸው ሁነቶች ውስጥ ደግሞ ጥምቀት አንደኛው ነው። ከጣሊያን ሀገር ጥምቀትን በጎንደር ለማክበር የመጡ ጎብኝዎች “ኢትዮጵያ የምታስደንቅ ሀገር ናት” ብለዋል።
በጎንደር ያገኘናቸው ስቴፈን ሜክሌኒ ወደ ኢትዮጵያ ስመጣ የመጀመሪያዬ ነው፤ የመጣሁት ከባለቤቴ ጋር ነው፤ እያየሁት ባለሁት ነገር እየተደነቅኩ ነው፤ ግን ኢትዮጵያን በሙሉ አይቼ ተረድቻታለሁ ማለት አይደለም ብለዋል።
ከቀናት በፊት የልደት በዓልን በላሊበላ እንዳከበሩ የነገሩን ስቴፈን በላሊበላ አስደናቂ ሃይማኖታዊ ሥርዓት እና ባሕል ተመልካቻለሁ ነው ያሉት።
በጎንደርም አስደናቂ አብያተ መንግሥታትን፣ አብያተ ክርስቲያናትን እና የጥምቀት ማክበሪያውን ሥፍራ አይቻለሁ፤ ውብ እና የምትገርም ከተማ ናት ብለዋል። በጥምቀት በዓል ደግሞ የበለጠ ድንቅ ነገር እንደምመለከት ተስፋ አለኝ ነው ያሉት።
ከዚህ በኋላ ኢትዮጵያን ደጋግሜ እጎበኛለሁ፤ ድንቅ ድንቅ ሥፍራዎችንም አያለሁ፤ ወደ ሀገሬ ስመለስም ሌሎች እንዲጎበኟት እጋብዛለሁ ብለዋል። ኢትዮጵያ በሌሎች ሀገራት ሊታዩ የማይችሉ ታሪካዊ፣ ተፈጥሯዊ እና ባሕላዊ ሃብቶች እንዳሏትም ገልጸዋል።
ሌላኛዋ ከጣሊያን የመጡት ሲሊቫ ቦዛሊ ኢትዮጵያን ለመጀመሪያ ጊዜ እንደተመለከቱ ገልጸዋል። ጥምቀትን ለመጀመሪያ ጊዜ በጎንደር ሊያከብሩ መኾናቸውንም ተናግረዋል። ባየሁት ነገር በጣም ተደስቻለሁ፤ የሰው የእንግዳ አቀባበልም የሚገርም ነው ብለዋል።
በኢጣሊያ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ሃይማኖታዊ ሥርዓት በስፋት ይካሄዳል፤ ሃይማኖታዊ አስተምህሮው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጋር ተቀራቢነት አለው፤ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ሃይማኖታዊ አከባበር እና ሥርዓት ግን ለየት ያለ ነው ብለዋል። ይህም ይመስለኛል ተወዳጅ እና ለጎብኝዎች ሳቢ ያደረጋት ነው ያሉት።
ወደፊት በተደጋጋሚ ኢትዮጵያን እጎበኛለሁ፤ ምክንያቱም ኢትዮጵያ ታላቅ እና ታሪካዊት ሀገር ናት ብለዋል። ሌሎች ጎደኞች እና ዘመዶቼ ኢትዮጵያን እንዲጎበኟት እጋብዛቸዋለሁ ነው ያሉት።
በመላው ኢትዮጵያ በጣሊያንኛ ቋንቋ እንደሚያስጎበኝ የነገረን ይሳቅ አብዱረዛቅ ጎንደር እንግዶቿን በድምቀት እየተቀበለች ነው ብሏል። ሃይማኖታዊ በዓላት የውጭ ሀገር ጎብኝዎችን እንደሚስቡም ተናግረዋል። ኢትዮጵያ ካላት ሃብት እና ጸጋ አንጻር ግን ከዚህ የበለጠ ጎብኝዎችን መሳብ አለብን ነው ያለው።
ኢትዮጵያ ባላት ሃብት እየተጠቀመች አይደለም፤ እኛም እየተጠቀምን አይደለም፤ ታላቅ ጸጋ ያላት ሀገር ናት ጸጋዋን በደንብ መጠቀም አለብን ብሏል። ኢትዮጵያ የሚታይ ብዙ ሃብት ስላላት የውጭ ሀገር ጎብኝዎች ከጊዜ ወደጊዜ እየጨመረ መምጣቱን ተናግሯል። ከዚህ በላይ ለመጠቀም እና ጎብኝዎችን ለመሳብ ሰላማችንን መጠበቅ አለብን ሲልም ጠቁሟል።
ሰላማችን ከጠበቅን ጸጋ ስላለን ጎብኝዎች ከዚህ በላይ ይጨምራሉ፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ እንግዳ የመቀበል የካበተ ባሕል አለው ነው ያለው። ለቱሪዝም ከዓመት እስከ ዓመት መዘጋጀት እንደሚገባም ተናግሯል።
ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleየጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) መልዕክት፦
Next article“የእንሶስላችን ትዝታ”