“ሰይ ሰይ” የጎንደር ጥምቀት ልዩ ትዕይንት!

0
ባሕር ዳር: ጥር 10/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ጥምቀት በሁሉም አካባቢዎች የሚከበር በዓል ቢኾንም በጎንደር ደግሞ ልዩ መልክ አለው።
“ሰይ ሰይ” የተባለው የወጣቶች የወንዶች ባሕላዊ ጨዋታ ጥምቀትን በጎንደር ልዩ ድምቀት ከሚሰጡት ክዋኔዎች ውስጥ አንዱ ነው። ሰይ ሰይ በተለይም በማዕከላዊ ጎንደር ዞን በደንቢያ እና ዙሪያው የሚዘወተር ባሕላዊ የወንዶች ጨዋታ ነው።
ቃሉ “እሰይ እሰይ” እንኳን አደረሰን ለማለት እንደኾነ የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ባሕል ቱሪዝም እና ስፖርት መምሪያ መረጃ ያረጋግጣል።
የሰይ ሰይ አጨዋወት ስልትን ከልምዳቸው እየቀዱ ሊያጫውቱን ከአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ጋር ቆይታ ያደረጉት አቶ ታከለ አለሙ እንደሚሉት ጨዋታው ወንዶች ታቦታትን ሲያጅቡ ክብ ሠርተው የሚከውኑት ዓይነ ግቡ የጥምቀት ዕለት ትዕይንት ነው ብለውናል።
የጨዋታው ተዋናዮች ቀጠን ያለ ሽመል የያዙ ሁለት ሰዎች ይኾናሉ። ሽመሉን በተጋጣሚ ሰውነት ላይ ለማሳረፍ የሚደረግ ፍጹም ሰላማዊ እና ለጉዳት የማይዳርግ ፍልሚያ ነው ብለዋል አቶ ታከለ።
ጨዋታው ሰውነትን በተቃራኒ ተጫዋች ሽመል ላለማስነካት የያዙትን ሽመል ግራ እና ቀኝ በፍጥነት እያዟዟሩ መመከትን መሠረት ያደረገ እንደኾነም ገልጸውልናል።
በትክክል መመከት ያልቻለው ተጫዋች የተጋጣሚው ሽመል ከጭኑ አካባቢ ያርፍበታል። ተጋጣሚን ለጉዳት በሚያጋልጥ ቦታ ላይ ሽመል ማሳረፍ በጨዋታው ሕግ የተከለከለ ነው። ጭን አካባቢ ላይ ብቻ ነው ማሳረፍ የሚቻለው ይላሉ። ይሄኔ በተለምዶ “ተገለበ” ይባላል ብለዋል።
ሽመሉ በተጫዋቾች ሰውነት ላይ የሚያርፈው ጉዳት በሚያደርስ መልኩ አይደለም። ለመንካት ያክል “ቸብ” ነው የሚደረገው።
ሕጉን ጠብቆ የተጋጣሚው ሽመል ያረፈበት ሰው ተሸናፊ ይኾንና ከጨዋታ ውጭ ይኾናል። አሸናፊው ቦታውን ይዞ እየተጎማለለ ሌላ ጀግና ተጫዋች ያማትራል።
ይሄኔ በሁለቱ ተጫዋቾች ዙሪያ ክብ ሠርተው ሲታደሙ ከነበሩት በርካታ ሰዎች ውስጥ “እኔ አለሁ ጀግና” የሚል ሌላኛው ወጣት “ሰይ ሰይ” የሚል ድምጽ ያሰማና ዘሎ ወደ መጫወቻ አውድማው ይገባል ሲሉ ክዋኔውን አስረድተውናል።
ተጋጣሚውም “ሰይ ሰይ” ብሎ ይቀበለውና የያዙትን ዱላ በመላ ሰውነታቸው ዙሪያ በፍጥነት እያዟዟሩ ራስን የመከላከል፣ ይልቁንም የተገኘውን ክፍተት ተጠቅሞ የተጋጣሚን ሰውነት በሽመሉ ለመንካት ብርቱ ጥረት የሚደረግበት ትዕይንት ይቀጥላል። ሽመሉ ያረፈበት ተሸናፊ ይወጣል፤ አሸናፊውን ለመጋጠም ሌላ ይገባል ብለዋል።
ሰዎች ቢፈራረቁ እንኳን ገላውን በሽመል ማስነካት ያልቻለ ወጣት የጨዋታው ኮከብ ከመኾኑም በላይ እንደጀግና ይቆጠራል። በጨዋታው ዙሪያ ከሚታደሙት ቆነጃጅቶች ውስጥ የተወረወረ የፍቅር ሎሚም ሊያርፍበት ይችላል ነው ያሉን አቶ ታከለ።
ሰይ ሰይ የፍቅር እና የደስታ ጨዋታ ነው። አጋጣሚ ኾኖ በተጫዋቾች መካከል አላግባብ ግጭት ቢፈጠር እንኳን እዚያው ላይ ይፈታል እንጅ ውሎ የሚያድር ቂም በፍጹም የተጠላ ነው ብለዋል። ተጋጣሚዎቹ በፊት የማይተዋወቁ ከኾኑ ጨዋታቸውን ሲጨርሱ ተዋውቀው እና ለዓመት ተቀጣጥረው እንደሚለያዩም አቶ ታከለ ከልምዳቸው አጋርተውናል።
“ይህ ተናፋቂ የጥምቀት ጨዋታ ባለፉት ሁለት የጥምቀት በዓላት በሰላም እጦት ምክንያት ደብዝዞብን ነበር፤ በዚህ ዓመት ግን በተለመደው ድምቀት ለመጫወት የሚያስችለንን ሰላም በማግኘታችን ተደስተናል፤ ለጨዋታውም ከወዲሁ ተዘጋጅተናል” ነው ያሉን።
በምሥራቅ ደምቢያ ወረዳ ባሕል፣ ቱሪዝም እና ስፖርት ጽሕፈት ቤት የቱሪስት መዳረሻ ልማት ባለሙያው አንተነህ ገነቱ እንዳሉት ሰይ ሰይ በተለይም በከተራ እና በጥምቀት ዕለት በብዛት የሚተገበር ባሕላዊ የወንዶች ጨዋታ ነው ብለዋል።
ጨዋታው የበዓል ደስታ እና ሀሴትን ለመግለጽ እሰይ እንኳን አደረሰን በማለት የማይተዋወቁ ሰዎችም ጭምር በጋራ የሚጫወቱት፣ ጥምቀትም የሚደምቅበት፣ የአብሮነት ጨዋታ ነው ብለዋል።
ሰይ ሰይ የአጨዋወት ሕግ እንዳለውም ገልጸውልናል። መጫወቻ ሽመሉ ቀጭን መኾን አለበት፤ ሊጎዳ በሚችል ኃይልም መምታት ክልክል ነው። ራስ፣ እግር፣ መገጣጠሚያ እና ሌሎችም በቀላሉ ሊጎዱ በሚችሉ የሰውነት ክፍሎች ላይ ሽመሉን ማሳረፍ አይቻልም ነው ያሉት።
ቀድሞ ጥላቻ ያለባቸው ሰዎች የጥምቀት ቀን ሰይ ሰይ ከተጫወቱ ቂም በቀላቸው ከዚያ ቀን ጀምሮ እንደሚያሽርም ባለሙያው ገልጸዋል።
ይህ ባሕላዊ የአብሮነት ጨዋታ የበለጠ እንዲያድግ እና ለትውልድ እንዲተላለፍ እየተሠራ ስለመኾኑም ነግረውናል።
ለዚህም የባሕል ቱሪዝም እና ስፖርት ተቋሙ ከሃይማኖት አባቶች እና አጥኝዎች ጋር በጋራ በመኾን ባሕላዊ ጨዋታው ሁነኛ የቱሪስት መስህብ እንዲኾን በሚያስችል መልኩ እየተሠነደ እንደሚገኝም ገልጸውልናል።
ዘጋቢ፦ አሚናዳብ አራጋው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleየጽንፈኛውን የሚዲያ ልሳን ሲመራ የነበረው ጋዜጠኛ ኤልያስ ደባሱ የሰላም ጥሪን ተቀበለ።
Next articleየጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) መልዕክት፦