
ባሕር ዳር፡ ጥር 10/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የጽንፈኛውን የሚዲያ ልሳን በዋነኝነት ሲመራ የነበረው ጋዜጠኛ ኤልያስ ደባሱ የሰላምን ጥሪ በመቀበል እጁን ለምሥራቅ ዕዝ ሰጥቷል። “የአማራ ጥያቄ በትጥቅ ትግል እናስመልሳለን” በማለት እሱና ጓደኞቹ “አማራ ተበደለ፣ ተጨቆነ” ብለው ነፍጥ አንስተው ለሁለት ዓመታት ጫካ መቆየታቸውን ተናግሯል።
በነበረው ቆይታም በፊት ይሠራበት የነበረውን አሻራ ሚዲያ ጫካ ላይ ሆኖም በዋና ማኔጀርነት በመምራት መቀመጫውን ጎጃም በማድረግ የተለያዩ ሀሰተኛ መረጃዎችን በፌስ ቡክ፣ በዩቱውብ፣ በቲክቶክ፣ በቴሌግራም፣ በዋትስ አፕ፣ በቲውተር እና በሳተላይት ቴሌቪዥን ፕሮግራም ጭምር ሲያስተላልፍ መቆየቱን ገልጿል።
በቅርቡም ራሱን የአማራ ፋኖ ብሔራዊ ኃይል ብሎ የተደራጀውን ቡድን ፕሮፖጋንዳ አሻራ ሚዲያን እንደ ልሳን በመጠቀም ይመራ ነበር።
በተጨማሪም ሌሎች 12 የሚሆኑ የመገናኛ ብዙኀን የትጥቅ ትግሉ አጋር በመኾን የአማራ ሚዲያ ካውንስል የሚባል የሚዲያ አደረጃጀት ውስጥ ገብተው መረጃ ሲያሰራጩ ነበር። እሱም እጁን ለምሥራቅ ዕዝ እስከሰጠበት ድረስ አባል ሆኖ ሲሠራ መቆየቱን አስረድቷል።
ክልሉን ለማፍረስ እና ለማተራመስ ሲሠራ የነበረው አስራት ሚዲያ ከፈረሰ በኋላ እንደ አዲስ አሻራ ሚዲያን በማዋቀር በተለያዩ ዓለማት የሚገኙ የጽንፈኛው ቡድን አባላት ቦርድ አቋቁመው ስቱዲዮውን አሜሪካ በማድረግ የፕሮፖጋንዳ ጋጋታ በማኅበራዊ ሚዲያ በማሰራጨት ኅብረተሰቡን በተለይም ወጣቱን ላልተገባ የሕይወት መስዋዕትነት ሲያነሳሳ እንደነበር አጋልጧል።
መረጃ ቲቪ በተባለው ጣቢያም በስሩ በሚያስተዳድራቸው በርካታ ግለሰቦች ለጥቅም ሲሉ በሀሰተኛ አካውንት በተከፈቱ በርካታ የፕሮፖጋንዳ ማሰራጫ አውታሮች በመጠቀም አፍራሽ ዜናዎች እንዲሰራጩ ሲያደረግ እንደነበር ተናግሯል።
ጋዜጠኛ ኤልያስ ደባሱ እንዳለው እሱን የመረጃ ምንጭ ያደረጉ በርካታ ሚዲያዎች የተዛቡ እና መንግሥትን የሚያጥላሉ ዜናዎችን ይሠሩ ነበር። ከነዚህም መካከል በመአዛ መሐመድ የሚመራው ሮሀ ሚዲያ፣ በሙሉጌታ አንበርብር የሚዘወረው ኢትዮ 251፣ በቃሉ አላምረው እና በላይ ማናዬ የሚያስተዳድሩት ኢትዮ ኒውስ፣ ምናላቸው ስማቸው የሚዘግብበት ግዮን ሚዲያ፣ መረጃ ቴሌቪዥን እና ሌሎችም ቀጥታ እሱን የመረጃ ምንጭ እያደረጉ የተዛባ መረጃ ሲያሰራጩ እንደነበረ ተናግሯል።
እነዚህ ሚዲያዎች በሠራዊታችን ላይ ያልተገባ ስም በመስጠት እና “በሉት ግደሉት” በማለት ኅብረተሰቡን በማነሳሳት ሀገር ሲያምሱ እንደነበርም ዘርዝሯል።
ጽንፈኛው በጎጥ ተከፋፍሎ እርስ በእርሱ ሳይስማማ ማኅበረሰቡን “ግብር ክፈሉ” እያለ ሲያስገድድ ነበር፤ የተለያዩ የመሰረተ ልማት ሥራዎች እንዳይሠሩ በርካታ ሕገ ወጥ ተግባራትንም ፈጽሟል ሲል አብራርቷል።
ጽንፈኛው “እታገልለታለሁ” ላለው ኅብረተሰብ ትውልድ ይቅር የማይለው ኢ ሰብዓዊ ድርጊት ፈጽሟል፤ ኅብረተሰቡን በራሱ ቀየ አዋርዷል፤ የመንግሥት ሠራተኞችን ገድሏል፤ ሴቶችን አስገድዶ ደፍሯል፤ ካህናትን ክብራቸውን ዝቅ አድርጎ አንገላቷል፤ ወጣቶችንና አርሶ አደሮችን በዓደባባይ ረሽኗል ነው ያለው ጋዜጠኛ ኤሊያስ።
የጽንፋኛው የሥልጣን ሰንሰለት አብዛኛው ሀብት ለማካበት በዘረፋ ላይ ተጠምዷል። በአደረጃጀቱ አመራር ያሉትም አብዛኞቹ ከማረሚያ ቤት የወጡ ናቸው። በመሆኑም ትግሉ የተበታተነ እና የኤርትራን ፍላጎት ለማሳካት የሚለፋ ነው ብሏል።
ጽንፈኛው ከኤርትራ የሚላክለትን የጦር መሳሪያ በሕወሃት በኩል እያሰረገ ክልሉን ላልተገባ ትርምስ እና ቀውስ ዳርጎታል ነው ያለው። አሁን ላይ ተደራጅቶ ሠራዊታችንን ሊዋጋ ቀርቶ በየሰፈሩ እና ጉራንጉር ውስጥ በመግባት ሕይወቱን ለማትረፍ እየጣረ እንደሚገኝ አረጋግጧል።
እኔም ይህ የሕዝቤን ስቃይ ያባባሰው የትጥቅ ትግል እንደማያዋጣ አምኜ መንግሥት ያወጣውን የሰላም ጥሪ በመቀበል እጄን ሰጥቻለሁ ነው ያለው። እንደኔ ተታለው ጫካ ገብተው ሕዝባቸውን እየወጉ ያሉ ጓደኞቼ የሰላም አማራጩን ተቀብለው እንዲገቡ እና የበደሉትን ሕዝብ እንዲክሱ ጥሪዬን አቀርባለሁ፤ ባሰራጨዋቸው ትክክል ያልሆኑ መረጃዎች ተሰልበው ጽንፈኛውን ለተከተሉም ይቅርታ እጠይቃለሁ ብሏል። ዘገባው የምሥራቅ ዕዝ ነው።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
