”ባሕር ዳር ሁልጊዜ ጽዱ እንድትኾን እንሠራለን” ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው

5
ባሕር ዳር: ጥር 10/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር የጥምቀት በዓልን ምክንያት በማድረግ የጽዳት ሥራ አከናውኗል።
የባሕር ዳር ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው በጽዳት ዘመቻው ከነዋሪዎች ጋር በመገኘት የተሳተፉ ሲኾን መልዕክትም አስተላልፈዋል።
ባሕር ዳር ከተማን በበዓላት ቀን ብቻ ሳይኾን ሁልጊዜም ጽዱ እና ምቹ ለማድረግ እየተሠራ መኾኑን ነው የተናገሩት።
የጥምቀት በዓልን አስመልክቶ የከተማው መሪዎች ከሕዝቡ እና ከጽዳት ሠራተኞች ጋር በመኾን ጽዳትን ማከናወናቸው የከተማዋን ውበት እና ሳቢነት የሥራቸው አካል በማድረግ መኾኑን ገልጸዋል።
“ባሕር ዳር ሁልጊዜ ጽዱ እንድትኾን እንሠራለን” ያሉት አቶ ጎሹ የጥምቀት በዓልም በስኬት እንዲከበር ሁሉም የከተማዋ የኅብረተሰብ ክፍሎች ኀላፊነታቸውን እንዲወጡ መልእክት አስተላልፈዋል።
በዓሉ በሰላም እንዲከበር ሕዝቡ አካባቢውን በንቃት እንዲጠብቅ እና ከጸጥታ ኃይሎች ጋር በመተባበር እንዲሠራም ጠይቀዋል።
የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪ የኾኑት ሀጂ ተዘራ አበበ በጽዳት ሥነ ሥርዓቱ ተሳትፈዋል። በዓሉ የክርስቲያኖች ቢኾንም የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮችም በወንድሞቻቸው በዓል ደስተኛ መኾናቸውን ገልጸዋል። የሃይማኖት መለያየት በወንድማማችነት ተከባብሮ ከመኖር እንደማያግድም ተናግረዋል። ለባሕር ዳር ውበት ተባብረን እንሥራ የሚል መልዕክትም አስተላልፈዋል።
በጽዳት ሥራ ሲሳተፉ ያገኘናቸው ወጣት ተመስገን መዝገቡ እና ሃይማኖት መኳንንት በየዓመቱ በጽዳት ሥራ እንደሚሳተፉ ገልጸዋል።
ባሕር ዳር ከተማን ጽዱ እና ውብ ለማድረግ ከበዓላት ቀን ውጭም መሥራት እንደሚያስፈልግ እና ለማጽዳት ዝግጁ መኾናቸውን ተናግረዋል።
ዘጋቢ፦ ዋሴ ባዬ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleደንቢ ኢኮ ሎጅ ተመረቀ።
Next articleየተወዳጁ አርቲስት ነጻነት ወርቅነህ የአስከሬን ሽኝት ሥነ-ሥርዓት እየተካሄደ ነው።