
ባሕር ዳር: ጥር 10/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ዘመን የማይሽርሽ ንግሥት ነሽና ዓለም ይቀናብሻል፤ የታሪክ አምባ ነሽና ሕዝብ ይደነቅብሻል፤ የሥልጣኔ ማማ ነሽና ያየሽ ይገረምብሻል፤ ትውልድ ይኮራብሻል፤ ሕዝብ ይመካብሻል፤ አብዝቶም ያደንቅሻል።
ኢትዮጵያ ትደምቅብሻለች፤ ኢትዮጵያ ትኮራብሻለች፤ ኢትዮጵያ ታሪኳን ታሳይብሻለች፤ ኢትዮጵያ ከፍታዋን ትገልጥብሻለች፤ ኢትዮጵያ ኢትዮጵያዊነትን ታስተምርብሻለች ጎንደር።
ጎንደር የሰርግ ቤት ትመስላለች ደስታና ፍስሃ የሚበዛባት፤ ጎንደር ብራና ትመስላለች ታሪክ የሚነበብባት፤ ጎንደር ባሕር ትመስላለች ፍልስፍና እና ጥበብ የሚቀዳባት፤ ጎንደር ንጉሥ ትመስላለች አጀብ የማይጠፋባት፤ ጎንደር እናት ትመስላለች ማጉረስ እና ማልበስ የማይሰለቻት፣ ልጅ የሚያጌጥባት፤ ሁሉም እናት የሚላት፤ እማማ እያለ የሚንሰፈሰፍላት፤ ጠርቶ የማይጠግባት፤ ርቆ የሚናፍቃት፤ አብሯት እያለ የሚሳሳላት።
ጎንደር አባት ትመስላለች ልጅ የሚመካባት፤ ጎንደር መሶብ ትመስላለች ሁሉም በአንድነት የሚመገቡባት፤ ጎንደር የዋርካ ጥላ ትመስላለች የደከመ የሚያርፍባት፤ የተጣላ የሚታረቅባት፤ አስታራቂ አበው የሚቀመጡባት፤ ጎንደር ተራራ ትመስላለች የሥልጣኔ ከፍታ የሚለካባት፤ ጎንደር የማትነጥፍ ምንጭ ትመስላለች ታሪክ፣ ዕውቀት፣ እሴት፣፣ ሃይማኖት፣ ፍልስፍና እና ጥበብ የሚጠጣባት።
ጎንደር ንጋት ትመስላለች የሥልጣኔ ጮራ የሚወጣባት፤ ጎንደር ኮኮብ ትመስላለች በጨለማ የሚያበሩ ጀግኖች የተፈጠሩባት፤ ጎንደር መሰሶ ትመስላለች ሀገር በጽናት የቆመችባት፤ ጎንደር መሠረት ትመስላለች ኢትዮጵያዊነት የጸናባት።
ምስጢራዊ ተራራዎች የከበቧት፤ የተባረኩ ምንጮች የፈለቁባት፤ የተወደዱ ዋርካዎች ጥላ የኾኗት፤ አያሌ ነገሥታት በከበረው ዙፋን የተቀመጡባት፤ አምረው የተሠሩ አብያተ ክርስቲያናት እና አብያተ መንግሥታት ከጌጥ የላቀ ጌጥ የኾኗት፤ ከግርማ የላቀ ግርማ የሰጧት፣ የሰማይና የምድሩን ምስጢር የሚፈቱ ሊቃውንት የመሉባት፤ ሙያን ያስተማሩ እምቤቶች የተወለዱባት፤ ሀገርን ከነፍስ በላይ የሚወዱ ጎበዛዝት እትብታቸው የተቀበረባት ጎንደር ሁልጊዜም ትናፈቃለች። ሁልጊዜም ትወደዳለች፤ ሁልጊዜም ትሞገሳለች።
በጥምቀት ደግሞ በሕዝብ ትመላለች፤ በኢትዮጵያውያን ትዋባለች። እልፍኞቿን እና አዳራሾቿን በእንግዳ ትመላለች። ይህች ዓለም የሚቀናባት፣ ኢትዮጵያ የምትደምቅባት ከተማ በታቦታቱ እየተባረከች፤ በሊቃውንቱ እየተመራች፤ በጠቢባኑ እየመከረች የጌታን ጥምቀት ታከብር ዘንድ በሰፊው እልፍኝ፣ ሰፊውን ድግስ ደግሳለች። መስጠት የማይሰለቹ እጆቿ፣ እንግዳ ተቀብለው በቃን የማይሉ እልፍኞቿ እንግዶቿን አቅፈዋል፤ በፍቅር ተቀብለዋል።
የጎንደር ጎዳናዎች ለታቦታቱ መረማመጃ ተሰናድተዋል፤ የጎንደር ሊቃውንት በጥበብ እየተራቀቁ ለጌታቸው ጥምቀት ተዘጋጅተዋል፤ የጎንደር እናቶች ለእልልታ እና ለምስጋና ጓጉተዋል። የጎንደር ወጣቶች ታቦታቱን ያጅቧቸዋል።
ጥምቀትን በጎንደር ማክበር ድንቅ ነገር ነው። በአርባ አራት ታቦታት መባረክ እጹብ ነው። አሰግድ ተስፋዬ ጎንደር የአፍሪካ መናገሻ በተሰኘው መጽሐፋቸው ጥምቀትን በጎንደር ማክበር መባረክ ነው ይላሉ።
በጥምቀት ከተራ በጎንደር አድባራት ደወሉ ሲያቃጭል፤ ነጋሪቱ ሲጎሰም፤ መለከቱ ሲነፋ ሰማይ የተከፈተች ትመስላለች። ምድርም የሰማዩን ሙሽራ ለመቀበል የተዘጋጀች ትመስላለች። የጎንደር ጥምቀት እጹብ ድንቅ ነው።
ይሄን ድንቅ ሥርዓት ተመለከቱ፤ በአራባ አራት ታቦታት መካከል ተመላለሱ። ከክብሩም ተቋደሱ። ኑ! ጥምቀትን በጎንደር!
በታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
