ለጥምቀት ድምቀት የወጣቶች ሚና

3
ባሕር ዳር: ጥር 10/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ‎ጥምቀት በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አማኞች ዘንድ በየ ዓመቱ በድምቀት የሚከበር ሃይማኖታዊ በዓል ነው።
ታቦታት ከመንበራቸው ወጥተው ወደ ባሕረ ጥምቀት በመውረድ ሕዝቡን የሚባርኩበት በዓልም ነው።
‎በጥምቀት ጊዜ ወጣቶች ታቦታትን በዝማሬ እና በእልልታ በማጀብ፣ መንገዶችን በማጽዳት፣ የታቦታትን መሄጃ ምንጣፍ በመሸከም እና በማሥተባበር ያለእረፍት ሢሠሩ ማየት የተለመደ ተግባር ነው።
በቡድን በመኾን ተመሳሳይ ባሕላዊ አልባሳት ለብሰው በዓሉን ሲያደምቁት ይታያሉ።
ይህም በሃይማኖቱ ተከታዮች ዘንድ መንፈሳዊ እርካታን የሚሰጥ ነው። በረከትን የሚያሰጥ ተደረጎም ይወሰዳል።
‎ወጣት ማረልኝ ዳኛው በባሕር ዳር ከተማ ነዋሪ ነው። በጥምቀት በዓል በብዙ ተግባራት እንደሚሳተፍም ገልጾልናል። አሁንም ከገና በዓል ማግስት ጀምረው እየተዘጋጀ መኾኑን ነግሮናል።
‎ወጣቶች በጥምቀት ታቦታት እና ምዕመናን የማያልፉበትን መንገድ እና የባሕረ ጥምቀት ቦታውን በማጽዳት፣ ለክብረ በዓሉ በማመቻቸት ሥራዎችን ማከናወናቸውን ተናግሯል።
ተግባራትን የሚሠሩት የቤተክርስቲያኗ አባቶች በሚሰጡን መመሪያ መሠረት ነው። ከሥራቸው ቀደም ብለው ውይይቶችን እንዳደረጉም ገልጾልናል።
‎‎በዓሉ በሰላም እንዲከበር ከማኅበረሰቡ እና ከጸጥታ አካላት ጋር በጋራ እንደሚሠሩም አንስቷል። መንገዶች እንዳይጨናነቁ ተለዋጭ መንገዶችን ማመቻቸት የተግባራቸው አካል እንደኾነም ነው የነገረን።
‎ወጣቶች በዚህ ተግባራቸው ከመንፈሳዊ አገልግሎት በተጨማሪ ሃይማኖታቸውን እንዲጠብቁ እና ባሕላቸውን እንዲያከብሩ ዕድል ይፈጥራል ብሏል። የተግባቦት ክህሎት የሚያዳብሩበት እና መንፈሳዊ ጥንካሬ የሚያገኙበት መኾኑንም ጠቅሷል።
‎ወጣቶች ለአገልግሎት ሲወጡ እና መለያየትን አስወግደው ነው፤ ይህ ደግሞ ለሀገር ግንባታ አስተዋጽኦው ከፍተኛ መኾኑን ነው የገለጸው። በቱሪስት መስህብነትቱም ኢኮኖሚውን እንደሚያነቃቃ አንስቷል።
‎ሀገር በአባቶች የተሠራች፣ በወጣቶች ትከሻ ላይ ያለች እና ለትውልድ የምትተላለፍ ናት ያለው ወጣት ማረልኝ ወጣቶች በበዓሉ በሚሠሩት ተግባር ለሕጻናት መልካም አርዓያ እንደሚኾኑ አመላክቷል።
‎በጥምቀት በዓል እንደሚደረገው ርብርብ ሁሉ የተቸገሩ ወገኖችን ማገዝ ላይ እየተሠራ ስለመኾኑም ተናግሯል።
‎በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የማኅበረ ቅዱሳን የግዮን ወረዳ ማዕከል የወጣቶች አሥተባባሪ ጌታሰው ሸጋው የጥምቀት በዓል ትውፊቱን ጠብቆ ለማክበር የወጣቶች ሚና ከፍተኛ መኾኑን ተናግሯል።
‎ሰላሙን በማሥተባበር፣ በእጀባ እና በምስጋና አገልግሎት፣ በጽዳት እና በሌሎች ተግባራት እንደሚከውኑ ገልጾልናል። ለዘንድሮው በዓልም ወጣቶች በሰፊው መዘጋጀታቸውን ጠቁሟል።
‎ወጣቶች ለቤተክርስቲያን በሚሠሩት ሥራ ለሕጻናት አርዓያነታቸውን የሚያሳዩበት እና በረከት የሚያገኙበት በዓል እንደኾነም አንስቷል።
‎የቤተክርስቲያን አገልግሎት በኅብረት የሚፈጸም ነው። ይህንን ትብብር በሌሎች የልማት እና ማኅበራዊ ተግባራትም እንዲቀጥል መሥራት ያስፈልጋል ነው ያለው።
‎ወጣቶች በዓሉን ሲያከብሩ ባሕላዊ ክዋኔዎች እና አለባበሳቸው ከቤተክርስቲያኗ ሥርዓት ባልወጣ መንገድ እንዲኾንም መልዕክት አስተላልፏል።
‎ዘጋቢ፦ ፍሬሕይወት አዘዘው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleየባህል ልብሶች ድምቀት ለጥምቀት!
Next articleየበገና ምስጢር ‎