
ባሕር ዳር፡ ጥር 10/2018ዓ.ም (አሚኮ) የጥምቀት በዓል በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አማኞች ዘንድ በታላቅ ድምቀት የሚከበር ሃይማኖታዊ በዓል ብቻ ሳይኾን የሀገሪቱን ባሕላዊ ውበት፣ አንድነት እና ኢኮኖሚያዊ መነቃቃት የሚያሳይ ታላቅ መድረክ ነው፡፡
ጥምቀት ሲቃረብ የኢትዮጵያ አደባባዮች በነጭ ድባብ ይሞላሉ፡፡ ከሃይማኖታዊ ሥርዓቱ ባሻገር የሀገር በቀል ጨርቃጨርቅ ውጤቶች የሚታዩበት፣ የኢትዮጵያውያን የጥበብ ክህሎት ለዓለም የሚገለጥበት የፋሽን አደባባይ ይመስላል፡፡
በበዓሉ ዋዜማ እና በዕለቱ ሴቶች በእጅ የተሸመነ የሀበሻ ቀሚስ በመልበስ ይደምቃሉ፡፡ በቀሚሶቹ ግርጌ ላይ የሚገኙ የተለያዩ ጥልፎች እና ዲዛይኖች የሀገሪቱን ባሕላዊ ብዝኀነት ያንጸባርቃሉ፡፡
የበሃል ቀሚስ ለማሠራት ሱቅ ላይ አሚኮ ያገኛቸው ወይዘሮ መሰረት ይማም “የሀገር ልብስ ሳለብስ ጥምቀትን ማሳለፍ አይመቸኝም” ይላሉ፡፡ በዚህ ምክንያት ለስድስት ዓመታት በየዓመቱ አዳዲስ የባሕል ልብሶችን ለራሳቸው እና ለቤተሰቦቻቸው እንዳሠሩ ነው የተናገሩት፡፡
ዛሬም የሀገር ባሕል ልብስ ዋጋው ውድ ቢኾንም “ለጥምቀት ያልኾነ ቀሚስ ይበጣጠስ ብየ እስከቤተሰቦቸ ተመሳሳይ የሀገር ባሀል ልብስ ለማሰራት ነው የመጣሁት” ብለውናል፡፡
ሌላኛዋ ሲገዙ ያገኘናቸው ወይዘሮ ያልጋነሽ አጥናፉ ጥምቀትን ለረጅም ዓመታት የሀገር ባሕል ልብስ ከልጆቻቸው ጋር ለብሰው ደምቀው እንደሚያከብሩት ነግረውናል። በየዓመቱ ዋጋው እየተወደደ ቢመጣም ጥምቀት ያለ ቀሚስ ስለማይደምቅ ከልጆቸ ጋር “ፏ ” ብየ ለመዋል አስቤ ነው የምገዛው ብለውናል፡፡
ወጣት ታደለ ዘውዱ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ወጣቶች በቡድን ተመሳሳይ ልብስ በመልበስ በዓሉን በድምቀት እያከበሩ እንደኾነ ነግሮናል፡፡
ወጣት ታደለ ከጓደኞቹ ጋር በመኾን በየዓመቱ ከ60 እስከ 75 የሚኾን የሀበሻ ልብስ በማሰራት በዓሉን በጋራ በደመቀ ሁኔታ እንደሚያከብሩ ገልጾልናል፡፡ “የምናሠራበት ዋጋ ከዓመት ዓመት እየጨመረ ቢመጣም በዓመት አንዴ የምናከብረው በዓል በመኾኑ ደስ ብሎን እናሠራዋለን” ነው ያለን፡፡
የበዓል ልብስ ስፌት ባለሙያ አቶ ደጀኔ የሻነው እንዳሉት ከበዓሉ ወራት በፊት ጀምሮ ሸማኔዎች፣ ስፌት ቤቶች እና ጠላፊዎች ሥራቸው ይጨምራል። አቶ ደጀኔ ከጥምቀት በዓል ጋር ተያይዞ የሥራ ጫና ይበዛል፡፡ ያም ቢኾን ተጨማሪ ምሽትን በመጠቀም የሰዎችን ትእዛዝ ለማድረስ ከፍተኛ ጥረት እንደሚያደርጉ ነግረውናል፡፡
አቶ ደጀኔ የሀገር ልብሶች ዋጋቸው እንዲወደድ የሚያደርገው ከጥጥ መልቀም ጀምሮ እስከ ሽመና እና ጥልፍ ድረስ በሰው ጉልበት የሚሠራ በመኾኑ እና የማስጌጫ ክሮች ከውጭ መምጣታቸው እንደኾነ ጠቁመዋል።
የባሕል ፋሽን ዲዛይነር ወይዘሮ ፀአዳ ምትኩ የሀገር ባሕል ልብሶች በሙያ ተሻሽለው እየተሠሩ መምጣታቸው የሕዝብ ፍላጎት እንዲጨምር ማድረጉን ይናገራሉ። በዚህም ተጠቃሚ መኾናቸውን ጠቅሰዋል።
የባህል ልብስ ሰፊ አቶ ኪሩቤል መብራቱ
በጥምቀት በዓል ወቅት አብዛኛው የማኅበረሰብ ክፍል መልበስ የሚፈልገው እና የሚያዘው በጥልፍ የሚሠራውን ባሕላዊ ልብስ ነው ብለዋል፡፡
ባለፉት ሁለት እና ሦሥት ዓመታት ገብያው የተቀዛቅዞ እንደነበር እና በዚህ ዓመት ግን የተሻለ እንቅስቃሴ መኖሩን ነግረውናል፡፡
በተለይ የሴቶች የሀበሻ ቀሚስ ከ5 ሺህ ብር ጀምሮ እስከ 120 ሺህ ብር ዋጋ ሊያወጣ የሚችል ሥራ እንደሚያሠሩ ተናግረዋል፡፡ በዚህም በዘርፉ የሚሳተፉት ሁሉ ተጠቃሚ እንደኾኑ ነው የሚገልጹት።
ዘጋቢ፡- ሰናይት በየነ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
