
ባሕር ዳር: ጥር 10/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በየዓመቱ ጥር 11 ቀን የጥምቀት በዓል ይከበራል፡፡ የጥምቀት ዋዜማውም የከተራ በዓል በመባል ይታወቃል፡፡
ከተራ የሚለው ቃል ከተረ ከሚለው የግዕዝ ቃል የመጣ ሲኾን መገደብ ወይም ማቆር የሚል ትርጉም እንዳለው የሃይማኖቱ አስተምህሮት ይተነትናል።
በሃይማኖቱ አስተምህሮ እንደሚገለጸው ኢየሱስ ክርስቶስ በመጥምቁ ዮሐንስ ለመጠመቅ ከገሊላ ወደ ፈለገ ዮርዳኖስ ወንዝ ያደረገውን ጉዞ የሚያስታውስ መንፈሳዊ ትርጉምም ያለው ነው።
በዚህ ዕለት ታቦታት በካሕናት እና በምዕመናን ታጅበው ከመንበራቸው በመነሳት ሥርዓተ ጥምቀቱ ወደ ሚከናወንበት ሥፍራ ይጓዛሉ። ታቦታቱ የሚያርፉበት እና የሚያድሩበት ቦታም ባሕረ ጥምቀት በመባል ይታወቃል፡፡
በማዕከላዊ ጎንደር ሀገረ ስብከት የጎንደር መንበረ መንግሥት መድኃኒዓለም ቤተ ክርስቲያን የአራቱ ጉባዕያት ምክትል መምህር መምህር ዘላለም ሀዲስ ከተራ የሚባለው ክብ የኾነ ወይም ዙሪያውን የታጠረ ማለት ነው። መነሻው ኢየሱስ ክርስቶስ በተጠመቀ ጊዜ ማየ ዮርዳኖስ በመንፈስ ቅዱስ እሳትነት ተከብባ ስለነበር ያንን ምስጢር የሚገልጽ ስለመኾኑ አብራርተዋል።
በጥምቀት ዋዜማ ታቦታቱ በአቅራቢያቸው ወደሚገኝ ወንዝ ወርደው በወንዙ ዙሪያ ከትመው ያድራሉ። ከዚህ መነሻነት ከተራ የሚባለው የታቦታቱን በወንዙ ዙሪያ ከቦ ማደር፤ ሲነጋም ምዕመናን በወንዙ ዙሪያ ክብ ሠርተው መቆማቸውን የሚገልጽ መኾኑን አስረድተዋል።
በከተራ የታቦታት ወደ ወንዝ መውረድ ሃይማኖታዊ ታሪክ አለው ብለዋል መምህሩ፡፡ በዋዜማው ታቦታቱ ወደ ወንዙ መውረዳቸው ኢያሱ ታቦተ ጽዮንን ለካህናት አስይዞ ዮርዳኖስን በተሻገረ ጊዜ የካህናቱ እግር ውኃ ሲነካ ጥምቀት ኾኖ እንደተቆጠረላቸው መምህሩ ገልጸውልናል። በኋላም ኢየሱስ ክርስቶስ በዮርዳኖስ ወንዝ ተጠምቆ አማናዊ ጥምቀትን መሠረተልን ነው ያሉት።
ታቦታት ከጥምቀተ ባሕሩ ከደረሱ በኋላ ሌሊቱን ሙሉ የሃይማኖት አባቶች እና ምዕመናን በጸሎት እና በምስጋና ያድራሉ። ሌሊቱን ሙሉም ማኅሌተ ጥምቀት ተብሎ የሚጠራው መንፈሳዊ ክዋኔ በካህናቱ ይቀርባል ብለዋል።
ታቦታት ወደ ወንዝ የሚወርዱት የአማናዊ ጥምቀት ምስጢርን ለማስረዳት እንደኾነ ነው የገለጹት። በሌላም በኩል ታቦተ ሕጉ ወደ ወንዙ መውረዱ የክርስቶስን ከሰማያት መውረድ የሚገልጽ ሲኾን ወደ መንበሩ መመለሱ ደግም ማረጉን (እርገቱን) ያስረዳል ነው ያሉት።
ዘጋቢ:- አሰፋ ልጥገበው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
