
ጎንደር: ጥር 09/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በጎንደር ከተማ የፋሲለደስ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የማስፋፊያ ሕንፃ ግንባታ ምረቃ ላይ የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበልን ጨምሮ የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ምክትል ኀላፊ መኳንንት አደመ፣ የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ቻላቸው ዳኘው፣ የሀገር ሽማግሌዎች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
ሕንፃው ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ እንደተደረገበትም ተገልጿል።
በጎንደር ከተማ የሚገኘው በቀድሞው ስያሜው ቀዳማዊ ኃይለስላሴ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የአሁኑ የፋሲለደስ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ከ1934 ዓ.ም ጀምሮ የመማር ማስተማር ሥራውን እየከወነ ይገኛል።
የፋሲለደስ ድምጽ ማኅበር ሥራ አሥፈፃሚ ኮሚቴ ሰብሣቢ ዓባይ ዘለቀ ሕንፃው ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ እንደተደረገበት አረጋግጠዋል።
ትምህርት ቤቱ ባለ ሁለት ወለል ሲኾን 34 መማሪያ ክፍሎችን እና 5 ልዩ ልዩ አገልገሎት የሚሰጡ ቢሮዎችን የያዘ የማስፋፊያ ሕንፃ ነው።
በ2012 ዓ.ም የማስፋፊያ ግንባታ ኮሚቴ ተቋቁሞ ወደ ሥራ የተገባ ሲኾን በግንባታ ሥራው በውጭ ሀገር የሚኖሩ የቀድሞ የፋሲለደስ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎችን ጨምሮ የጎንደር ከተማ ነዋሪዎች እና ሌሎችም ባለድርሻዎች ተሳታፊ ኾነዋል።
የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ቻላቸው ዳኘው ትምህርት ቤቱ በርካታ ምሁራንን ያፈራ መኾኑን ገልጸዋል። የትምህርት ቤቱን ታሪካዊነት እና ውጤታማ የመማር ማስተማር ሂደቱን ለማስቀጠል በውጭ ሀገር የሚኖሩ የቀድሞ የትምህርት ቤቱ ተማሪዎች እና ሌሎችም ባደረጉት እገዛ ለውጤት መብቃቱን ተናግረዋል።
የሕንፃ ግንባታውን ለማጠናቀቅ ስድስት ዓመት የፈጀ መኾኑንም ገልጸዋል።
የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ምክትል ኀላፊ መኳንንት አደመ በትምህርት መስኩ የኅብረተሰቡ ተሳትፎ ሚናው ጉልህ መኾኑ የታየበት እንደኾነ አስረድተዋል።
ይህንን ተሞክሮም በሌሎች አካባቢዎች ማስፋፋት እንደሚገባ ጠቅሰዋል። የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ የትምህርት ቤቶች ደረጃ መሻሻል ወሳኝ መኾኑንም ተናግረዋል። የማስፋፋፊያ ሕንፃ ግንባታው የትምህርትን ጥራት ለመጠበቅ ወሳኝ ሚና እንዳለውም አመላክተዋል።
ትምህርት አዲስ ምዕራፍ መክፈቻ እና የሀገር ዕድገት ማስቀጠያ ሁነኛ መንገድ ነው ያሉት የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል የፋሲለደስ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የማስፋፊያ ሕንፃ ግንባታ የነገ ሀገር ተረካቢዎችን ለመቅረጽ የሚያስችል መኾኑን አስገንዝበዋል።
የሕንፃ ግንባታው የተቆርቋሪነት ስሜት ማሳያ መኾኑን የጠቀሱት ሚኒስትሩ መላኩ አለበል በቀጣይም ትምህርት ቤቱን በማዘመን ብቁ ተማሪዎችን ለማፍራት መሥራት እንደሚገባ ተናግረዋል።
በመርሐ ግብሩ ለሕንፃ ግንባታው ድጋፍ ላደረጉ ተቋማት እና ግለሰቦች የዕውቅና እና ምሥጋና መርሐግብር ተካሂዷል።
ዘጋቢ፦ ቃልኪዳን ኃይሌ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
