
ደሴ: ጥር 09/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በደቡብ ወሎ ዞን ኩታበር ወረዳ በ2018 በጀት ዓመት ተሠርተው የተጠናቀቁ የተለያዩ የመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶች ተጠናቅቀው ለአገልግሎት ክፍት ኾነዋል።
የኩታበር ወረዳ ዋና አሥተዳዳሪ ጀማል ይመር ወረዳው በሰሜኑ ጦርነት ጉዳት ከደረሰባቸው ወረዳዎች ውስጥ አንዱ እንደነበር አስታውሰዋል። ከዓለም ባንክ በተመደበ ከ440 ሚሊዮን ብር በጀት በተሠራ የመልሶ ማቋቋም ተግባር የተለያዩ የልማት ሥራዎች ተከናውነዋል ብለዋል።
በ11 ቀበሌዎች 20 ብሎክ ትምህርት ቤቶች፣ በሰባት ቀበሌዎች የጤና ጣቢያዎች እና የውኃ ተቋማት ተገንብተው ለአገልግሎት ክፍት መኾናቸውን ገልጸዋል።
የአማራ ክልል በጦርነት ጉዳት የደረሰባቸው አካባቢዎች መልሶ ማቋቋምና መልሶ ማልማት ፈንድ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አባተ ጌታሁን (ዶ.ር) የተለያዩ አጋዥ ድርጅቶችን በማሥተባበር እና በክልሉ ፋይናንስ ከ13 ቢሊዮን ብር በላይ በመመደብ በክልሉ 1ሺህ 370 የልማት ፕሮጀክቶች በመጠናቀቅ ላይ ይገኛሉ ብለዋል።
በኩታበር ወረደ ከ440 ሚሊዮን ብር በላይ በመመደብ የተሠሩ የልማት ፕሮጀክቶች በሰሜኑ ጦርነት ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባቸው መኾናቸውን ገልጸዋል።
የደቡብ ወሎ ዞን ዋና አሥተዳዳሪ አሊ መኮንን በቀጣይም የተለያዩ የበጀት ምንጮችን የማሥተባበር እና የመደገፍ ሥራዎች ይሠራሉ ብለዋል።
በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የማኅበራዊ ዘርፍ አሥተባባሪ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር) “የተጠናቀቁ የልማት ፕሮጀክቶች የማኅበረሰቡ የረጅም ጊዜ ጥያቄዎችን የመለሱ ናቸው” ብለዋል።
በሰሜኑ ጦርነት ጉዳት የደረሰባቸው ተቋማትን መልሶ በመገንባት ሂደት የተመደበውን በጀት በአግባቡ በመጠቀም በአጭር ጊዜ በዚህ መልኩ የተጠናቀቁ ፕሮጀክቶቸን በማየቴ ደስተኛ ነኝ ነው ያሉት።
ዘጋቢ:- ደምስ አረጋ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
