ጎርጎራ ኢኮ ሪዞርት-የትውልዱ አሻራ!

7
  • ባሕር ዳር፡ ጥር 09/2018ዓ.ም (አሚኮ) በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ ᎐ር) ሃሳብ አመንጭነት ከሚከናወኑ የገበታ ለሀገር ፕሮጀክቶች መካከል በጣና ሐይቅ ምዕራባዊ ዳርቻ የሚገኘው ጎርጎራ፣ በደቡብ ምዕራብ ሸዋ የሚገኘው ወንጭ እና በኮንታ የሚገኘው ኮይሻ ይገኙበታል፡፡

የጎርጎራ ኢኮ ሪዞርት ግንባታ ተፈጥሯዊ ይዘቱን በጠበቀ መልኩ ስለመገንባቱ ያዩ መስክረውለታል።

ሪዞርቱ በተለይም የሰሜን ኢትዮጵያን የቱሪዝም መዳረሻነት ይበልጥ በማስፋት እና በማጠናከር ረገድ ጉልህ ሚና እየተጫወተም ይገኛል።

በማራኪ ገጽታ እና በመልክዓ ምድራዊ አቀማመጡ በኢትዮጵያ አስደናቂ ከሚባሉ ስፍራዎች መካከል አንዱ የኾነው የጎርጎራ ኢኮ ሪዞርት ድሮም በገናና ታሪኳ እና በተፈጥሯዊ ሃብቷ የደመቀችውን ጎርጎራ በገበታ ለሀገር ፕሮጀክት ደግሞ ይበልጥ ማሳመር፣ መሞሸር እና ማስዋብ ተችሏል።

የጎርጎራ ኢኮ ሪዞርት ጎንደር የኢትዮጵያ መናገሻ በነበረችበት ወርቃማ የታሪክ ዘመን በነበራት ከፍታ ላይ ተጨማሪ ጌጥ ኾኖ እንዳጎናጸፋት ይነገራል።

ከባሕር ዳር -ጎንደር -ራስ ደጀን ድረስ ለሚደርሰው በታሪክ፣ በሃይማኖት እና በባሕል ለታደለው አካባቢ የጎርጎራ ኢኮ ሪዞርት ተጨማሪ ውበትን አላብሶታል።

ከጎንደር ገናና ታሪክ ጋር የምትተሳሰረው እና በአንድነት የምትጠቀሰው ጎርጎራ ለዚህ ዘመን ትውልድ ትልቅ ሃብት እና የሃብት ምንጭ ማድረግ ተችሏል።

ጎርጎራ ኢኮ ሪዞርት ከከተሞች ባሻገር ከጥንታዊ የጣና ወደቦች ጋር ትስስር እንዲፈጠር እና አካባቢው እንዲለማ በር የከፈተም ነው፡፡

ሪዞርቱ በክልሉ የሚገኙ ሌሎችንም ያልተገለጡ አካባቢዎች መግለጥ እና ማሳየት እንደሚገባም አመላክቷል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ᎐ር) የጎርጎራ ኢኮ ሪዞርት በተመረቀበት ወቅት ሲናገሩ ፕሮጀክቱ በፈተናዎች ውስጥ የተሠራ ደማቅ የትውልድ አሻራ ነው፤ ሪዞርቱ ሙሉ በሙሉ በሀገር ልጆች የተገነባም ነው፤ ይህም በራስ አቅም ሌሎች ፕሮጀክቶችን ለመገንባትም አቅም እና ዕውቀት ይዞ የመጣ ነው ሲሉ ተናግረውም ነበር።

ሪዞርቱ የኢትዮጵያን ውበት ለዓለም በመግለጥ የሀገር ቱሪዝምን ለማሳደግ እና ለአካባቢው ማኅበረሰብ የሥራ ዕድሎችን በመፍጠር ረገድ ሚናው ከፍተኛ መኾኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ መናገራቸው አይዘነጋም።

የጎርጎራ ኢኮ ሪዞርት ግንባታ የካቲት 28/ 2013 ዓ.ም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ሲያስጀምሩ ጎርጎራ የባሕር ዳር እና የጎንደር የቃልኪዳን ቀለበት የትስስር ማዕከል እንደኾነ ገልጸውም ነበር።

በሙሉጌታ ሙጨ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የለውጥ ሥራዎች ዋነኛ ማጠንጠኛ የዳኝነት አገልግሎትን በማሻሻል የኅብረተሰቡን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ነው” አቶ ዓለምአንተ አግደው
Next article“የተጠናቀቁ የልማት ፕሮጀክቶች የማኅበረሰቡን የረጅም ጊዜ ጥያቄዎች የመለሱ ናቸው” ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር)