
ባሕር ዳር፡ ጥር 09/2018ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በየደረጃው የሚገኙ ፍርድ ቤቶችን የ2018 የበጀት ዓመት የስድስት ወራት የሥራ አፈጻጸም እየገመገመ ነው።
ዛሬም የማዕከላዊ ጎንደር ከፍተኛ ፍርድ ቤት እና የጠቅላይ ፍርድ ቤት ጎንደር ምድብ ችሎት የስድስት ወራት የሥራ አፈጻጸም ገምግሟል።
የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ቸርነት ተገኘ በተያዘው በጀት ዓመት የተሻለ የሥራ አፈጻጸም ተመዝግቧል ብለዋል፡፡
ለዚህም ከመሥከረም 20/2018 ዓ.ም እስከ መሥከረም 30/2018 ዓ.ም የተካሄደው የዳኞች ጉባኤ የፈጻሚዎችን የሥራ ተነሳሽነት ከፍ እንዲል ማድረጉ ዋናው ምክንያት እንደኾነ ገልጸዋል፡፡
የዳኝነት አገልግሎት አሰጣጥ ጥራትን፣ ቅልጥፍናን፣ ተደራሽነትን እና ወጥነትን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ የለውጥ ሥራዎች ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ መኾኑን ተናግረዋል። ለሰው ሃብት ልማት ሥራ ልዩ ትኩረት በመስጠት ከጎንደር ዩኒቨርሲቲ ጋር ተቀራርቦ በመሥራት የተለያዩ ሥልጠናዎችን ሲሰጡ መቆየታቸውን አንስተዋል።
የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የትራንስፎርሜሽን ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ሀናን አበበ የትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ ሲታቀድ ምቹ የሥራ አካባቢዎች አለመኖር፣ የዳኝነት አገልግሎት አሰጣጡ በኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ የተደገፈ አለመኾን፣ አሳሪ የኾኑ የሕግ ማዕቀፎች መኖር እና የሰው ሃብት ልማትን በተመለከተ የነበሩ ችግሮችን መለየታቸውን ገልጸዋል። ችግሮቹን በመሠረታዊነት ለመቅረፍ በተከታታይነት በተሠሩ ሥራዎች ተስፋ ሰጭ ውጤቶች መመዝገባቸውን ገልጸዋል፡፡
የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የአይሲቲ ዳይሬክተር መኳንንት አገኘሁ (ዶ.ር) የዳኝነት አገልግሎት አሰጣጡን በኢንፎርሜሽን እና ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ በማስደገፍ ተደራሽ፣ ግልጽ እና ለተገልጋዮች ምቹ ለማድረግ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ መኾኑን ጠቁመዋል።
የዲጂታላይዜሽን ሥራውንም እስከ ወረዳ ፍርድ ቤቶች ለማድረስ ዕቅድ ተይዞ እየተሠራ ነው ብለዋል።
የዲጂታላይዜሽን ሥራውን በውጤታማነት ለመተግበር የሚያስችሉ ግብዓቶችን የማሟላት ሥራ፣ የሕግ እና የአሠራር ማዕቀፎች ዝግጅቶች ተጠናቅቀው በትግበራ ላይ እንደሚገኙም ገልጸዋል፡፡
የውይይቱ ተሳታፊዎችም በፍርድ ቤቶች የተጀመሩ የለውጥ ሥራዎች ተጨባጭ ለውጥ እያሳዩ መኾናቸውን ተናግረዋል። ቀጣይነት እንዲኖራቸው ትኩረት ሰጥቶ መሥራት እንደሚገባ አመላክተዋል።
የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዝዳንት ሙሉዓለም ቢያዝን በበጀት ዓመቱ መጀመሪያ ላይ የዳኞች ጉባኤ መደረጉ የፈጻሚዎችን የሥራ ተነሳሽነት ከፍ ማድረጉን ገልጸዋል።
ከሥነ ምግባር ጋር በተያያዘ የተነሱ ጉዳዮችን ለመቅረፍ እና ተጠያቂነትን ለማስፈን ግልጽነትን የሚያመጡ የአሠራር ሥርዓቶችን በመዘርጋት ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ ይሠራል ነው ያሉት፡፡
የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ዓለምአንተ አግደው በየደረጃው የሚገኙ የክልሉን ፍርድ ቤቶች የዳኝነት አገልግሎት አሰጣጥ በመሠረታዊነት ለማሻሻል በማለም ሥር ነቀል የለውጥ ሥራዎች እየተሠሩ እንደኾነ ተናግረዋል።
በአጭር ጊዜ ውስጥም የዳኝነት አገልግሎት ቅልጥፍና፣ ግልጽነት፣ ጥራት፣ ተገማችነት እና ወጥነት በማምጣት ተስፋ ሰጭ ለውጦች ታይተዋል ነው ያሉት። ነገር ግን አሁንም ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች አሉ ብለዋል።
የተጀመሩት የለውጥ ሥራዎችን እስከ ወረዳ ፍርድ ቤቶች ድረስ ለመተግበር የሚያስችል እና ነባራዊ ዕውነታውን ያገናዘበ ፍኖተ ካርታ ተዘጋጅቶ በተለየ ትኩረት እየተሠራበት እንደሚገኝም አስገንዝበዋል፡፡
ፍርድ ቤቶች ፍትሐዊነትን ለማስፈን፣ የመጨረሻ የመብት ማስከበሪያ መኾናቸውን ለማስገንዘብ እና በኅብረተሰቡ ዘንድ ተቀባይነታቸውን ይበልጥ ከፍ ለማድረግ የሚያስችሉ ሥራዎች እየተሠሩ ነው ብለዋል።
የለውጥ ሥራዎች ዋነኛ ማጠንጠኛ የዳኝነት አገልግሎትን በማሻሻል የኅብረተሰቡን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ እንደኾነ ገልጸዋል፡፡
ይህንን ለማድረግ የፈጻሚዎችን አቅም ይበልጥ ለማሻሻል የሚያስችሉ የተለያዩ የሰው ሃብት ልማት ሥራዎች ላይ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ መኾኑን አብራርተዋል፡፡
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
