
ደሴ፡ ጥር 09/2018ዓ.ም (አሚኮ) “ባሕላችን ለሰላማችን” በሚል መሪ መልዕክት በደሴ ከተማ ባሕል እና ቱሪዝም መምሪያ አዘጋጅነት 17ኛው የባሕል እና ኪነጥበባት ፌስቲቫል እየተካሄደ ነው።
በፌስቲቫሉ የወሎ እና አካባቢው የተለያዩ ባሕሎች እና የኪነጥበብ ሥራዎች እየቀረቡ ነው። በተጨማሪም የወሎን የሃይማኖቶች የቆየ አብሮነት እና መልካም እሴት የሚያሳዩ ኹነቶች ለታዳሚያን ቀርበዋል።
አስተያየታቸውን ለአሚኮ ያጋሩ ታዳሚያን የፌስቲቫሉ መዘጋጀት ቱባ ባሕላቸውን ጠብቆ ለትውልድ ለማውረስ ምቹ ኹኔታ እንደሚፈጥር አንስተዋል።
ባሕልን እና ኪነጥበብን የሚያስተዋውቁ መድረኮች በየጊዜው ሊዘጋጁ ይገባል ነው ያሉት።
የደሴ ከተማ አሥተዳደር ባሕል እና ቱሪዝም መምሪያ ኀላፊ ትዕግስት አበበ የአካባቢውን ባሕላዊ እሴት እና ወግ ታሳቢ ባደረገ መልኩ ፌስቲቫሉ መዘጋጀቱን ተናግረዋል።
ባሕል ለዘላቂ ሰላም ራሱን የቻለ አስተዋጽኦ ያበረክታል ያሉት ኀላፊዋ በተለይም ባሕላዊ የሽምግልና ሥርዓት በተጠናከረ መልኩ ከተሠራበት ግጭቶች የከፋ ጉዳት ሳያስከትሉ በዘላቂነት እንዲፈቱ የሚያግዝ መኾኑን አንስተዋል።
ቱባ ባሕሎችን እንዳይጠፉ፣ እንዳይበረዙ እና ተጠብቀው ለትውልድ እንዲተርፉ ታሳቢ ተደርጎ ፌስቲቫሉ መዘጋጀቱን ጠቅሰዋል።
የደሴ ከተማ አሥተዳደር ምክትል ከንቲባ ሽመልስ ጌታቸው የባሕል እና ኪነጥበብ ፌስቲቫል መዘጋጀቱ የአካባቢውን የኪነ ጥበባት እንቅስቃሴ በማበልጸግ ለቱሪዝም መጎልበት ምቹ ኹኔታ እንደሚፈጥር አንስተዋል።
በርካታ መንፈሳዊ እና የባሕላዊ እሴቶች ስላሉ ሊሠራባቸው ይገባል ያሉት ምክትል ከንቲባው መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ እየሠራባቸው ካሉ ዘርፎች መካከል የቱሪዝም ዘርፉ አንዱ መኾኑን አስታውሰዋል።
ኹሉም ባለድርሻ አካል ባሕል እና ኪነጥበብን መንከባከብ እና ማስተዋወቅ ይጠበቅበታል ነው ያሉት። በፌስቲቫሉ ለአንጋፋ የኪነጥበብ ሰዎችም ዕውቅና ተሰጥቷል።
ዘጋቢ:- መስዑድ ጀማል
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
