የባሕር ዳር ከተማን የማዘመን ሥራ ቀጥሏል።

4

ባሕር ዳር፡ ጥር 9/2018ዓ.ም (አሚኮ) የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር የከተማዋን የትራንስፖርት ችግሮች ሊቀርፉ የሚችሉ 10 በኤሌትሪክ የሚሠሩ ዘመናዊ አውቶብሶችን ወደ ከተማዋ አስገብቷል። ከተማ አሥተዳደሩ ባሶችን ሥራ የማስጀመር መርሐግብር አካሂዷል።

በመርሐግብሩ የክልሉ ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደን ጨምሮ የከተማዋ ከፍተኛ መሪዎች ተገኝተዋል።

በመርሐግብሩ የባሕር ዳር ከተማ የትራንስፖርት ኢተንተር ፕራይዝ ሥራ አስኪያጅ ዘውዱ ዘለቀ እነዚህን የሕዝብ አውቶብሶች ወደ ከተማዋ ለማስገባት እና አገልግሎቱን ለመስጠት የሚያስችል ሥልጠና ለባለሙያዎች መሰጠቱን ተናግረዋል። በ23 የከተማዎ መዳረሻዎችም አገልግሎት ይሰጣሉ ነው ያሉ።

ከእነዚህም በተጨማሪ ማኅበረሰቡ በፊት ይከፍለው የነበረውን የትራንስፖርት ወጭ 30 በመቶ የሚቀንስ መኾኑንም ተናግረዋል።

የጣና እና የዓባይ ገጽታ የቱሪስት መዳረሻ የኾነችውን የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪዎች የቆየ የትራንስፖርት እንግልት ለመቅረፍ የሚያስችል ዘመናዊ የሕዝብ ማመላለሻ መኪኖችን በማስገባታችን እንኳን ደስ አላችሁ ያሉት የባሕር ዳር ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው ናቸው።

ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው አንድን ከተማ ዘመናዊ ከሚያስብለው ውስጥ አንዱ ዘመናዊ የትራንስፖርት አገልግሎት መስጠት እንደኾነም ጠቁመዋል።

ዛሬም ከተማ አሥተዳደሩ 10 ዘመናዊ እና በኤሌክትሪክ የሚሠሩ አውቶብሶችን በማስገባት ሥራ ማስጀመራቸውን ጠቁመዋል።

አውቶብሶቹ ወደ ሥራ ከመግባታቸው በፊት ነዋሪዎች በትራንስፖርት ችግር ምክንያት በረጅም ሰልፎች ውድ ጊዜያቸውን ያባክኑ እንደነበርም ነው ያስረዱት።

ከዚህም በተጨማሪ ከተቀመጠው ታሪፍ በላይ እንዲከፍሉ ይገደዱም እንደነበር አስታውሰዋል።

እነዚህ የኤሌክትሪክ አውቶብሶች ከትራንስፖርት አቅርቦት ባለፈ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንዳላቸውም ጠቁመዋል።

በነዳጅ ላይ የሚባክነውን የውጭ ምንዛሬ ከማዳን ባለፈ ለተጠቃሚው ማኅበረሰብም በቅናሽ ታሪፍ አገልግሎ እንደሚሰጡ ነው ያስረዱት።

ከዚህ በፊት ያገለግሉ ከነበሩ 20 አውቶብሶች በተጨማሪ አዲሶቹ አውቶብሶች ለከተማዋ ማኅበረሰብ የተቀላጠፈ አገልግሎት እንዲሰጡ አስፈላጊ ምቹ ሁኔታዎችም ተፈጥረዋል ነው ያሉት።

አውቶብሶቹ ለሀገር ባለውለታ አቅመ ደካሞች እና ለአረጋውያን ነፃ አገልግሎት እንደሚሰጡም ነው የተናገሩት።

ይህ ጅምር ነው ያሉት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው በቀጣይም ቁጥራቸውን በማሳደግ ባሕር ዳርን በዘመናዊ የትራንስፖርት ትስስር እናሳልጣለን ብለዋል።

በመርሐግብሩ አውቶብሶቹን ያለምንም ችግር ከታሰበለት ቦታ እስኪደርስ አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት ዕውቅና እና ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።

ዘጋቢ፦ ሰናይት በየነ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን እና ደባርቅ ዩኒቨርሲቲ በጋራ ለመሥራት የሚያስችላቸውን ስምምነት ተፈራረሙ።
Next articleየባሕል እና ኪነጥበብ ፌስቲቫል ባሕል ሳይበረዝ ጠብቆ ለተተኪው ትውልድ ለማስተላለፍ ድርሻው የጎላ ነው።