
ጎንደር: ጥር 09/2018 ዓ.ም (አሚኮ) አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን እና ደባርቅ ዩኒቨርሲቲ በጋራ ለመሥራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርመዋል።
ስምምነቱን የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አሥፈጻሚ ጋዜጠኛ ሙሉቀን ሰጥዬ እና የደባርቅ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት አስማማው ዘገዬ (ዶ.ር) ናቸው የተፈራረሙት።
የአሚኮ ዋና ሥራ አሥፈጻሚ ጋዜጠኛ ሙሉቀን ሰጥዬ የጎንደር አካባቢ የቱሪዝም መዳረሻ በመኾኑ አሚኮ በተለያዩ ቋንቋዎች ዘገባዎችን በማሠራጨት ዘርፉን እያነቃቃ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
ደባርቅ ዩኒቨርሲቲ በዩኔስኮ በተመዘገበው የስሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ አካባቢ ያለ ተቋም መኾኑን ያነሱት ሥራ አሥፈጻሚው የቱሪዝም ዘርፉ ይበልጥ እንዲያድግ እና ዩኒቨርሲቲውን ውጤታማ በሚኾንበት ዘርፍ በጋራ እንሠራለን ነው ያሉት።
የዩኒቨርሲቲው የመማር ማስተማር፣ የጥናት እና ምርምር ሥራዎችን ውጤታማ እንዲኾኑ በትብብር እንደሚሠሩም ጠቅሰዋል።
አሚኮ የሬድዮ እና የቴሌቪዥን ሥርጭቶችን በጎንደር ቀጣና በማስጀመር ለኅብረተሰቡ መረጃ ሲያደርስ ቆይቷል ያሉት ጋዜጠኛ ሙሉቀን በምዕራብ ጎንደር ዞን በገንዳ ውኃ ከተማ የሬድዮ ጣቢያን ለመክፈት ወደ ሥራ መግባቱንም ተናግረዋል።
የደባርቅ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የምርምር ሥራዎቻቸውን የሚያጠናክሩ እና ሚዲያ ላይ እንዲሠለጥኑ አሚኮ በትኩረት እንደሚሠራ ገልጸዋል።
የደባርቅ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት አስማማው ዘገዬ (ዶ.ር) ከአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ጋር አብሮ ለመሥራት ስንፈልገው የነበር ነው፤ ዛሬ እውን ማድረግ ተችሏል ብለዋል። ደባርቅ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ ዘርፎች ትልቅ አበርክቶ እያደረገ እንደሚገኝም አስታውቀዋል።
ይህንን ለሕዝብ ለማስተዋወቅ ከአሚኮ ጋር በትብብር እንሠራለን ብለዋል።
በስምምነቱ የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን የደባርቅ ዩኒቨርሲቲን የመማር ማስተማር፣ የጥናት እና ምርምር፣ ማኅበራዊ ኀላፊነቶችን የተመለከቱ መረጃዎችን፣ ዘጋቢ ፊልሞችን እና ዜናዎችን ከዩኒቨርሲቲው ጋር በመተባበር ይሠራል ተብሏል።
የደባርቅ ዩኒቨርሲቲ የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ለሚጠይቃቸው የጥናት፣ የቴክኖሎጅ እና የሥልጠና ድጋፎችን ከራሱም ኾነ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ተባብሮ የሚሰጥ ይኾናል።
ዘጋቢ:- ያየህ ፈንቴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
