ወሎን የገለጠው የሎጎ ሐይቅ ሪዞርት

8

ባሕር ዳር፡ ጥር 09/2018ዓ.ም (አሚኮ) እነዛ ዳዋ የለበሱ የኢትዮጵያ ተስፋዎች አርቆ የሚያያቸው እና የሚገልጣቸው አጥተው ረዥም ዘመናትን አሳልፈዋል።

ምንም እንኳን ሀገርን በዕድገት ደረጃ በፍጥነት የማስፈንጠር አቅም ቢኖራቸውም ያስተዋላቸው ግን አልነበረም።

ጥቂት ድካሞች ቢጨመሩባቸው በርካታ ቱሪስቶችን የሚስቡት የቱሪዝም ሥፍራዎች ተገልጠው ይታዩ ዘንድ አንዳች ለውጥ ይፈልጋሉ። ይህንንም ተስፋ ሲጠብቁ ዘመናትን ተሻግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ሀገር ሲረከቡ ዳዋ ለብሰው የነበሩ እነዛ የሀገሪቱ የቱሪስት ሥፍራዎችን መግለጥ እንደ ዋና ሥራቸው አድርገው በመላው ኢትዮጵያ ተንቀሳቅሰዋል።

እስካሁንም ከነበሩበት ድባቴ ያወጧቸው የቱሪዝም ሥፍራዎች ሀገር እንደሚቀይሩ እና ሕዝብ ተስፋ ያገኘባቸው የሀገር የኢኮኖሚ ዋልታ መኾናቸው በርግጥም ታይቷል።

ከተገለጡት የሀገር ሃብቶች መካከል የወሎ ውበት እና ግርማ መግለጫ የኾነው እና በደቡብ ወሎ ዞን ሐይቅ ከተማ በሚገኘው ታሪካዊው የእስጢፋኖስ ሐይቅ ዳርቻ ላይ የሚገነባው የሐይቅ ሎጎ ሪዞርት ይገኝበታል።

ይህ ሐይቅ አሁን ላይ በግንባታ ሥራ ሂደት ቢኾንም ከወዲሁ ሕዝብ ተስፋ ጥሎበታል። በግንበታ ሂደትም ለበርካቶች እንጀራ መኾኑን ቀጥሏል።

የደቡብ ወሎ ዞን ባሕል እና ቱሪዝም መምሪያ ኀላፊ አስያ ኢሳ እንደነገሩን ሐይቅ እና አካባቢው የወሎ መገለጫ እና ተስፋ እንደኾነ አሻግረው ያዩት ብልሁ መሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ሃሳብ አመንጭነት የተጀመረው የሐይቅ ሎጎ ሪዞርት የወሎን ውበት ገልጧል ይላሉ።

ይህ የልማት ሥራ የቱሪዝም ቦታ ለኾነው ወሎ ምድር እና ለቱሪስት መዳረሻዎቹ ተስፋ ስለመኾኑ ነው የተናገሩት።

ቀደም ሲል ወሎ ላይ ያሉ የቱሪስት ቦታዎች ቱሪስቶች ሊቆዩባቸው የሚችሉ መሠረተ ልማቶች እንዳልነበሯቸው ገልጸው አሁን ለአብዛኞቹ የቱሪስት መዳረሻዎች በቅርብ ርቀት እየተገነባ ያለው የሐይቅ ሎጎ ሪዞርት ተስፋ ኾኗል ብለዋል።

ፕሮጀክቱ ከወዲሁ በቋሚ እና በጊዜያዊ የሥራ ዕድል ስለመፍጠሩ እና ሲጠናቀቅ ደግሞ ይበልጥ ጠቀሜታው ሰፊ ይኾናል ነው ያሉት።

ከዚህ ቀደም ለጥቂት ሰዓታት ገዳሙን እና በአካባቢው የሚገኙ የቱሪስት መዳረሻዎችን ለመጎብኘት ብቻ የሚመጡ ቱሪስቶች አሁን ባለው የሪዞርት አገልግሎት ለቀናት እንዲቆዩ በማድረግ የአካባቢውን ገቢ ያሳድጋል ነው ያሉት። ሪዞርቱ መንግሥት ከሠራቸው ሀገር አሻጋሪ የልማት ሥራዎች ውስጥ እንደሚጠቀስም ጠቁመዋል።

የሪዞርቱ መገንባት ለሐይቅ ከተማ እና ለደሴ አካባቢ የንግድ እንቅስቃሴ መነቃቃት ተስፋ ይዞ መምጣቱን የአካባቢው ነዋሪዎች ለአሚኮ ተናግረዋል።

ይህ ፕሮጀክት እንደ ኮይሻ እና ጎርጎራ ሁሉ፣ የመንግሥትን የቱሪዝም ሪፎርም የሚያሳይ ነው። በተለይም በሰሜኑ ጦርነት ምክንያት ተጎድቶ የነበረውን አካባቢው እና ምጣኔ ሃብታዊ እንቅስቃሴ መልሶ ለመገንባት ትልቅ ምልክት ተደርጎ ይወሰዳል ነው ያሉት።

በምሥጋናው ብርሃኔ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleባሕር ዳር ከተማ አሥተዳድር በቢኬጅ የተገጣጠሙ ዘመናዊ አውቶብሶችን ተረከበ።
Next articleአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን እና ደባርቅ ዩኒቨርሲቲ በጋራ ለመሥራት የሚያስችላቸውን ስምምነት ተፈራረሙ።