ንግሥቷን አጅቧት፣ ለክብሯ እጅ ንሷት።

33

ባሕር ዳር፡ ጥር 9/2018ዓ.ም (አሚኮ) ንግሥቷ ደግሳለችና እልፍኟን ሙሉላት፤ አጸዷን አድምቁላት፤ ጎዳናዎቿን ክበቡላት፤ ንግሥቷ አጊጣለችና አድንቋት፤ ንግሥቷ በቤተ መንግሥቱ ሰገነት ላይ ቆማለችና እጅ ንሷት፤ ተውባ ወጥታለችና አጅቧት። መለከቱን ንፉት፤ ነጋሪቱን ጎስሙት፤ እልልታ እና ኾታውን አቅልጡት።

ዘመናት የማይሽሩት ሙሽርነት፣ ዓመታት የማይለውጡት ንግሥትነት፤ እርጅና የማይረታው ውበት፣ አዝማናት የማያደበዝዙት ተወዳጅነት፤ የማይናወጽ ታላቅነት፤ የማይዝል ምሰሶነት፤ የሚያጸና ዋልታነት፤ የሚያበረታ ማገርነት ተችራለችና እየተወደደች ኖራለች፤ እየተወደደች አለች። በታሪክ ተከብራለች፤ በትውልድ ትደነቃለች ጎንደር።

ለዓመታት የማያረጅ ውበት እንደምን ያለ ውበት ነው? ለዓመታት የጸና ሙሽርነት እንደምን ያለ ምሹርነት ነው? ለዘመናት በማንነት መጽናት፣ በክብር መኖር፣ ከከፍታ አለመውረድ፣ በኢትዮጵያዊነት መድመቅ እንደምን ያለ ጥበብ ነው?

ጎንደር ቤተ መንግሥት ናት ነገሥታቱ የሚኖሩባት፤ ጎንደር አዳራሽ ናት ሕዝብ ሁሉ የሚሠባሠብባት፤ ጎንደር እልፍኝ ናት ሕብስት የሚመገቡባት፤ ወይን የሚጎነጩባት፤ ጎንደር ዋርካ ናት ተጠልለው የሚያርፉባት፤ ጎንደር ንግሥት ናት ሕዝቡ ሁሉ የሚከባት፣ ጎንደር ዙፋን ናት ንጉሥ የሚቀመጥባት፤ ጎንደር ዘውድ ናት ነገሥታቱ የሚከብሩባት፤ ጎንደር አክሊል ናት በቃል ኪዳን የሚጸኑባት፤ ጎንደር ሰይፍ ናት የሀገር ጠላት የሚቀጠባት፤ ጎንደር ጋሻ ናት የሀገር ጠላት የሚመከትባት።

ጎንደር እናት ናት ለልጆቿ ፍቅር መስጠት የማያልቅባት፤ ጎንደር የጥበብ ባሕር ናት ጥበብ የሚቀዳባት፤ ጎንደር ተራራ ናት የክብር ልክ፣ ከፍታ የሚገለጥባት፤ ጎንደር አድማስ ናት ከተራራው ማዶ ያለው ዓለም የሚታሰብባት፤ ጎንደር ገበያ ናት የተፈለገው ሁሉ የሚገኝባት፤ ጎንደር ገዳም ናት ጸሎት እና ምልጃ የማይቋረጥባት፤ ጎንደር ስዕል ናት የትናንት ማንነት የሚገለጽባት፤ ጎንደር መስታውት ናት የዛሬ መልክ የሚታይባት፤ ጎንደር ተስፋ ናት ነገን የሚመለከቱባት፤ ጎንደር ገመድ ናት ትናንት፣ ዛሬ እና ነገ የሚተሳሰሩባት፤ ጎንደር ካባ ናት ኢትዮጵያውያን በአንድነት የሚለብሷት፤ ጎንደር መሶበ ወርቅ ናት የኢትዮጵያዊነት ልዩ መልክ የሚገለጥባት፤ ጎንደር ማሕተም ናት ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊነት የሚረጋገጥባት።

ጎንደር ከከተማ ታልፋለች፤ ጎንደር ከሚታየው ውበትም ትሻገራለች፤ ጎንደር ከንግግር ትገዝፋለች፤ ከጽሑም ትልቃለች፤ ጎንደር ረቂቅ ናት፤ ጎንደር ያልተፈታች ምስጢር ናት።

በጎንደር አያሌ ነገሥታት ነግሠውባታል፤ የመናገሻ ከተማቸው አድርገዋታል፤ በአፍሪካ ገናናው ሥርዓት ተመሥርቶባታል፤ ያማረውም ቤተ መንግሥት ታንጾባታልና የአፍሪካ መናገሻ ይሏታል።

አሰግድ ተስፋዬ ጎንደር የአፍሪካ መናገሻ በተሰኘው መጽሐፋቸው ጎንደር የአፍሪካ መናገሻ ናት። ጎንደር የኢትዮጵያውያን ምሕንድስና የአዕምሮ ከፍታ የሚታይባት፤ የአፍሪካውያን ኩራት ናት ይላሉ። አሰግድ ጸሐፊ አዛዥ ሲኖዶስን ጠቅሰው ሲጽፉ ጎንደር በአህጉሩ ላመል ምንም የማይታጣባት ብለዋታል። ጎንደ የገነት አምሳያ የጥቁር ሕዝቦች ማማም ይሏታል።

ታምራት ወርቁ የመማጸኛ ከተማ በተሰኘው መጽሐፋቸው ጎንደር የመማጸኛ ከተማ ናት ይሏታል። የመማጸኛዋ ከተማ ማለትም ሰው በስሕተት ነፍስ ቢያጠፋ፣ ጥፋት ቢፈጽም ያ ድርጊቱ የተፈጸመበት ሰው ወገኖች ጥፋቱን ባጠፋው ሰው ላይ እርምጃ እንዳይወስዱበት ወይም ግድያ እንዳይፈጽሙበት የሚሸሸግበት ከተማ ማለት ነው።

ጎንደር ለምን የመማጸኛ ከተማ ተባለች? ቢሉ፤ ጎንደር የአርባ አራቱ አድባራት መገኛ ናትና ኅብረተሰቡ ለቤተ ክርስቲያን ካለው ፍቅር እና ለአባቶች ካለው ክብር የተነሣ በየትኛውም የሀገሪቱ ክፍል እና በከተማው የሚኖር ሰው በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ባጠፋው ጥፋት የከፋ ነገር እንዳይደርስበት በጎንደር ከሚገኙት አድባራት መካከል ወደ አንዱ፣ ካለበለዚያም ወደ ሊቀጳጳሱ ቤት በመሔድ ጥገኝነት ቢጠይቅ፤ ከጠየቀበት ጊዜ አንሥቶ ማንም አሳዳጅ አይፈልገውም፡፡ ጥገኝነት የሰጠው ደብርም ይሁን ጳጳስ አልያም እጨጌው ኀላፊነቱን ወስዶ በግቢው እንዲኖር ያደርገዋል፤ ተማጽኖውም ይሰምርለታል፤ ጸጸቱንም በዛው ይጨርሳል ይላሉ።

ጎንደር የጨነቀው ሰው የሚረጋጋባት፣ የሚማጸን ምላሽ የሚያገኝባት ከተማ ናትና የመማጸኛ ከተማ ትባላለች ነው የሚሏት።

ጎንደር ለዘመናት ወደ አጸዷ የሚመጡ እንግዶችን ሁሉ እምነትን፣ ብሔርን እና ጾታን ሳትመለከት በእንግድነት ስትቀበል ኖራለች፡፡ እነኾ ዛሬም እየተቀበለች ነው። የመማጸኛ ከተማም ኾና ዘልቃለች።

ጎንደር ሁልጊዜም ሙሽራ ናት የሰርግ ቤቷ የማይጎድልባት፤ ግርማ እና ሞገሷ የማይደበዝዝባት። ይህች ታሪካዊት፣ ጥንታዊት እና የተዋበች ኢትዮጵያዊት ሁልጊዜም ጎብኝዎች አይጠፉባትም። በወረኃ ጥር በጥምቀት ደግሞ ሙሽርነቷ ይደምቃል። ሚሊዮኖች ይከትሙባታል። ይማጸኑባታል።

አሁን ወርኃ ጥር ነው። ጥምቀት ደርሷል። “የጎንደር እልፍኝ አቤት ስፋቱ
የተመቸ ነው ቤተ መንግሥቱ” እንደተባለ እልፍኟን አሳምራ፤ በሰፊው ደግሳ እንግዶቿን እየተቀበለች ነው። ንግሥቷ የክብሯን ልብስ አስጊጣ እንግዶቿን እያቀፈች፤ ስሞት አፈር ስኾን እያለች እየተቀበለች እያጎረሰች፣ እያሳረፈች ነው።

ንግሥቷ ለጥምቀት ደግሳለችና ወደ ድግሱ ግስግሱ፤ በቤተ መንግሥቱ አጸድ ሥርም ተሠብሠቡ። ወደ እልፍኙም ግቡ። በጥምቀተ ባሕሩ ዙሪያም ተሰለፉ። በጥምቀተ ባሕሩ የሚታየውን ድንቅ ሃይማኖታዊ ሥርዓትም ተመልከቱ። ከበረከቱም ውሰዱ። የነገሥታቱን ታሪክ አድንቁ። ያማረውን እና የተዋበውንም እዩ።

ወደ ጎንደር አቅኑ ንግሥቷን አጅቧት፣ ለክብሯ እጅ ንሷት፤ በደስታዋ ተደሰቱ። በክብሯም ክበሩ።

በታርቆ ክንዴ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ(ዶ.ር) በአርቲስት ነጻነት ወርቅነህ ህልፈት የተሰማቸውን ሀዘን ገለጹ።
Next article“ሁሉም በአግባብ እና በሥርዓት ይሁን”ብጹዕ አቡነ አብርሃም