
ደብረ ብርሃን፡ ጥር 08/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በባለፉት ስድስት ወራት በከተማ አሥተዳደሩ ከ12 ቢሊዮን ብር በላይ ላስመዘገቡ 80 ባለሃብቶች የኢንቨስትመትን ፈቃድ መስጠቱን የደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት መምሪያ አስታውቋል፡፡
የኢንቨስትመንት ፈቃድ ከተሰጣቸው መካከል 60 በመቶ ያህሉ በግብርና ምርቶች ማቀነባበር ዘርፍ የተሰማሩ መሆናቸውን የመምሪያው ኀላፊ ብርሃን ገብረ ሕይወት ተናግረዋል። 30 ኢንዱስትሪዎች ፈጥነው ወደ ግንባታ መግባታቸውንም ጠቁመዋል፡፡
በተያዘው በጀት ዓመት 18 ኢንዱስትሪዎችን ወደ ምርት ለማስገባት ታቅዶ በስድስት ወራቱ ብቻ 14 ኢንዱስትሪዎች ወደ ማምረት ገብተዋል ነዉ ያሉት።
በደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር ወደ ማምረት ከገቡት ኢንዱስትሪዎች መካከል 43 ያህሉ ተኪ ምርቶችን በማምረት 42 ሚሊዮን ዶላር የውጪ ምንዛሬ ማስገኘታቸውን አንስተዋል። ስምንት ኢንዱስትሪዎች ደግሞ ምርቶቻቸውን ለውጪ ሀገራት ገበያ ማቅረብ ችለዋል ብለዋል።
እነዚህ ኢንዱስትሪዎች ለ6 ሺህ 400 ሰዎች የሥራ እድል ፈጥረዋል፡፡
በሌላ በኩል 18 ፋብሪካዎች ግንባታቸውን አጠናቅቀው ወደ ማሽን ተከላ ገብተዋል፡፡
የከተማ አሥተዳደሩ ትልቅ ሀገራዊ ፋይዳ ያላቸውን ኢንዱስትሪዎች ወደ ከተማዋ የመሳብ ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አቶ ብርሃን ገልጸዋል፡፡
ዘጋቢ፦ ደጀኔ በቀለ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
