
ጎንደር: ጥር 08/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በማዕከላዊ ጎንደር ዞን እና በጎንደር ከተማ አሥተዳደር የባሕል ፍርድ ቤቶችን ሥራ ማስጀመሪያ የግንዛቤ ማስጨበጫ ውይይት አካሂዷል።
የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ዓለምአንተ አግደው ባሕላዊ ፍርድ ቤቶችን ወደ ሥራ ለማስገባት እና ውጤታማ ለማድረግ እስከ ታች ደርሶ ውይይት ማድረግ አስፈላጊ በመኾኑ ውይይቱ መዘጋጀቱን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ሀገር በቀል ዕውቀት እና ባሕላዊ ሥርዓቶች ያሉባት ሀገር መኾኗን ያነሱት ፕሬዝዳንቱ ባሕላዊ የችግር መፍቻ ሥርዓቶች ተዘንግተው ቆይተዋል ነው ያሉት።
በአዋጅ ቁጥር 298/2017 መሠረት ባሕላዊ ፍርድ ቤቶችን እስከ ታችኛው እርከን ድረስ ለማውረድ መሠራቱ የባሕል እሴቶቻችንን ለማስቀጠል እና ኅብረተሰቡ በአካባቢው ፍትሕ እንዲያገኝ ለማስቻል ያለመ መኾኑን ነው የገለጹት።
ባሕላዊ ፍርድ ቤቶች የሕግ ማዕቀፍ ማግኘታቸው በባሕላዊ ፍርድ ቤቶች የሚወሰኑ ውሳኔዎች እውቅና የሚያገኙበት፤ ውሳኔያቸው የማይሻር እና የማይቆራረጥበት መኾኑንም ተናግረዋል።
የትውልዱ ስብዕና የሚገነባበት መኾኑን ያነሱት ፕሬዝዳንቱ ዜጎች ፍትሕ ለማግኘት የሚያወጡትን ወጭ የሚቀንስ ነው ብለዋል።
የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ቻላቸው ዳኘው እሴቶቻችንን ወደ ራሳችን ወስደን የችግራችን መፍቻ ቁልፍ ለማድረግ እየተሠራ ያለው ተግባር የሚመሰገን ነው ብለዋል። ክልሉ ከአጋጠመው ችግር እንዲላቀቅ የባሕል ፍርድ ቤቶች ወሳኝ እንደኾኑም አንስተዋል። ተግባሩን አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባም ገልጸዋል።
የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ቸርነት ተገኘ በዞኑ ሁሉም ቀበሌዎች የባሕላዊ ፍርድ ቤት ተግባራትን ውጤታማ ለማድረግ የግንዛቤ ማስጨበጫ እና ሌሎች ተግባራት እየተከናወኑ መኾኑን አንስተዋል።
የውይይቱ ተሳታፊ የሀገር ሽማግሌዎች ለባሕላዊ የሽምግልና ሥርዓት ሕጋዊ እውቅና መሰጠቱ እና ወደ ሥራ መገባቱ የሽምግልና ሥርዓቱን ውጤታማ እንዲኾን ያስችላል ነው ያሉት። ለውጤታማነቱም ጥረት እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።
ዘጋቢ:- ያየህ ፈንቴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
