
ባሕር ዳር: ጥር 08/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ዕዙ የ2018 ዓ.ም የግማሽ በጀት ዓመት የሥራ አፈፃፀሙን የዕዙ ከፍተኛ አመራሮች፣ የኮር እና የክፍለ ጦር አዛዦች እንዲሁም የዕዙ የመምሪያ ኀላፊዎች በተገኙበት ገምግሟል፡፡
በመድረኩም በዕዙ ስር ያሉ ክፍሎች ሪፖርታቸውን ከቀረቡ ሲኾን የነበሩ ጥንካሬዎችን እንዴት አስቀጥሎ መሄድ እንደሚገባ እና በቀጣይም መከናወን ስለሚገባቸው ተግባራት አቅጣጫ በመስጠት ሰፊ ውይይት ተካሂዷል።
የምሥራቅ ዕዝ ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል መሐመድ ተሰማ እንደተናገሩት ዕዙ ተልዕኮውን መነሻ በማድረግ በተሰማራባቸው በሶማሊያ ድንበር አልሸባብን የመደምሰስ እና የማዳከም ሥራ ከማከናወኑም ባሻገር በጎጃም ታጣቂ ቡድኑን እግር በእግር እየተከታተለ በመምታት ኅብረተሰቡ በሰላም ወጥቶ እንዲገባ እና የተጀመሩ መሰረተ ልማቶች እንዲቀጥሉ አድርጓል። ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠር በርካታ ተግባራትን ማከናወኑን አብራርተዋል፡፡
ምስራቅ ዕዝ በምስራቅ የሀገራችን ክፍልም ኾነ በጎጃም ዞኖች የሚያደርገውን የሕግ ማስከበር ኦፕሬሽን አጠናክሮ በመቀጠል ባለፉት 6 ወራት 2 ሺህ 439 የታጣቂ ቡድኑ አባላትን ደምስሷል፤ 425 አቁስሏል፤ 66 ታጣቂ እና 2 ሞርተር ማርኳል፡፡
በኦጋዴን የኢትዮጵያ ጠረፍን በመከላከል፣ የአልሸባብ ጥቃት በመመከት፣ የካሉብ የነዳጅ ፕሮጀክትን የመጠበቅ ግዳጆች እንዲሁም በምስራቅ እና በምዕራብ ሐረርጌ ዞኖች የኦነግ ሸኔን በገባበት ገብቶ በመደምሰስ በቀጣናው የተረጋጋ ሰላም መፍጠሩን ተናግረዋል፡፡
የኮንትሮባንድ እና ሕገወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውርን ከየአካባቢው የጸጥታ ኀይል ጋር በመቆጣጠር ውጤት የተገኘባቸው ኦፕሬሽኖችን መፈጸሙን አስረድተዋል፡፡
እንደ ዋና አዛዡ ገለፃ በምስራቁ ቀጣናም ኾነ በጎጃም የባዕዳንን ዓላማ ለማስፈፀም የሚንቀሳቀሱ የሀገር ውስጥ ባንዳዎች እና ተላላኪዎችን በንቃት ተከታትሎ በመደምሰስ፣ ሕዝባዊ በዓላት በሰላም እንዲከበሩ ከፍተኛ ሥራ ተሠርቷል ብለዋል፡፡
አሁን ላይ ታጣቂ ቡድኑ የሠራዊታችን ጠንካራ ምት መቋቋም አቅቶት አብዛኛው ታጣቂ እጅ እየሰጠ መኾኑን ጠቅሰው ኅብረተሰቡም ቡድኑ እስካሁን የዘረፈን እና የገደለን ይበቃናል ለማንም የሰፈር ሌባ አንገዛም በማለት በተለያዩ ሕዝባዊ መድረኮች ብሶቱን በመግለጽ እያወገዘው ይገኛል ነው ያሉት፡፡
ሕዝቡ ይህንን እኩይ ድርጊት ፈጻሚ በማውገዝ፣ የተሰገሰጉ ሴሎችን በማጋለጥ፣ ሎጂስቲክስ ባለመደገፍ፣ ተደራጅቶ አካባቢውን በመጠበቅ የራሱ ሰላም ባለቤት ለመኾን ሁሉም የየድርሻውን መወጣት ጀምሯል፡፡
በዚህም ኅብረተሰቡ ለምስራቅ ዕዝ ያለውን አክብሮት በመግለጽ ዕዙ በሚያደርጋቸው ስምሪቶች ሁሉ ከጎኑ እንደሚሰለፍ አረጋግጧል፡፡
ምስራቅ ዕዝ ከየክልሎቹ የፀጥታ ኀይል ጋር ባደረገው የተቀናጀ ስምሪት በድንበር፣ በምስራቁ የሀገራችን ክፍል፣ በባሕር ዳር፣ በሰሜን ጎጃም፣ በአዊ እና በምዕራብ ጎጃም ወረዳዎች እና ቀበሌዎች ተሰግስጎ የሕዝብን ሰላም ሲያደፈርስ፣ ሲዘርፍ እና ሲያወድም የነበረውን ኀይል የገባበት ገብቶ በመምታት ከፍተኛ ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ጉዳት አድርሶበታል፡፡
ሌተናል ጀኔራል መሐመድ በግምገማው ማጠቃለያ ላይ በአጭር ጊዜ ግዳጅ ማጠናቀቅ የሚያስችል የቀጣይ የስምሪት አቅጣጫ ሰጥተዋል።
አመራሮች ዕዙ በዘመናት ያካበተውን የፀረ-ሽምቅ ውጊያ አቅሙን ተጠቅሞ ሽብርተኞችን እና ፅንፈኞችን በመምታት የተገኘውን አንፃራዊ ሰላም አስተማማኝ ለማድረግ መሥራት እንደሚጠበቅ ማሳሰባቸውን ከምስራቅ ዕዝ ሚዲያ
የተገኘ መረጃ ያሳያል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
